የኢትዮዽያ ቡና ላኪዎች እሴት ጨምረው እንዲልኩ የአሰራር ማስተካከያዎች እየተደረጉ ነው

አዲ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የኢትዮዽያ ቡና ላኪዎች እሴት ጨምረው እንዲልኩ የአሰራር ማስተካከያዎች እና የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ነው ተብሏል።

የኢትዮዽያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ወደ ውጭ የሚላኩ ጥሬ ቡናዎችም የጥራት ደረጃቸው አስተማማኝ እንዲሆን ለማድረግ የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ነው።

ሞዬ ቡና ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፥ ቡናን በጥሬው ከመላክ ይልቅ ቆልጦ መላክን አዋጭ መሆኑን ተገንዝቦ፥ በዓመት እስከ 205 ሚሊየን ኪሎግራም ቡና መቁላት እና ማሸግ የሚችል ማሽንን ተክሎ ምርቶቹን ወደ አውሮፓና አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምስራቅም ይልካል።

ይሁን እንጂ ምርቶቹን አዘጋጅቶ የሚልከው በደንበኞች ፍላጎት በመሆኑ፥ ለውጭ ገበያ ብቁ የሆኑ ቡናዎችን ከኢትዮዽያ ምርት ገበያ መግዛት አለመቻሉ ለስራው እንቅፋት መሆኑን፥ የኩባንያው የአቅርቦት ክፍል ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ገልጸዋል።

የተቆላ ቡናን መግዛት የሚፈልጉ የውጭ ገዢዎች ቡናው የት፣ በምን ሁኔታ ውስጥ እንደበቀለ አጠቃላይ ታሪኩን ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ይህን አሰራር ግን የኢትዮዽያ ምርት ገበያ ባለስልጣን የሚከተለው አለመሆኑ ሌላው ማነቆ እንደሆነባቸውም ነው አቶ ኤፍሬም የተናገሩት፡፡

የኢትዮዽያ ቡና እና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳኒ ረዲ፥ እሴት ጨምረው የሚልኩ በላሃብቶችን አላሰራ የሚሉ መመሪያዎችን እና ደንቦችን የመፈተሽ ስራ በመሰራቱ ላኪዎች የሚያነሷቸውን ችግሮች በመቀረፍ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮዽያ ወደ ውጭ ከምትልከው ቡና በሰፋፊ የንግድ እርሻዎች የሚመረተው 10 በመቶው ብቻ ሲሆን፥90 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው በአነስተኛ አርሶ አደሮች ነው፤ ይህ ደግሞ ለጥራት መጓደል እና ለዘመናዊ መረጃ አያያዝ ስርዓት ማነቆ ሆኖ መቆየቱንም ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

የቡና ቆልቶ ላኪዎች ችግር የሆነውን የቡናን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻ ያለ ሙሉ ታሪክ አቀናጅቶ ማቅረብ ጥያቄን ለመመለስ፥ ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ ነው።

አቶ ሳኒ በኤክስፖርት ቡና ማደራጃዎችና ከአርሶ አደሩ ማሳ ጀምሮ የቡናን ጥራት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወን ቅድመሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብለዋል፡፡

እስከ ወረዳዎች ድረስ የተዘረጋ የጥራት ቁጥጥር ኮሚቴ በማቋቋምና በየደረጃውም ስልጠና የተሰጠ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመገንባት ላይ ባሉ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች ውስጥም፥ እሴት ጨምረው ወደ ውጭ ለሚልኩ ባለሀብቶች፥ የዓለም እሴት የተጨመረበት ቡና ገበያን ሰብረው ለመግባት ተወዳዳሪ እስኪሆኑ ጥራት ያለው ቡናን የሚፈልጉ በርካታ ገበያዎችን እንዲያገኙ መንግስት እገዛ ያደርጋል ሲሉ አቶ ሳኒ ተናግረዋል።

ሀገሪቱ በ2009 በጀት ዓመት 241 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ለመላክ፥ ከዚህም 941 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ያቀደቺ ሲሆን፥ ይህ ደግሞ ከአምናው የ30 በመቶ ጭማሪ አለው።

 

 

በትእግስት ስለሺ