የፈረንሳዩ አኮር ሆቴልስ በአዲስ አበባ ሶስት ሆቴሎችን ሊከፍት ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መቀመጫውን ፈረንሳይ ያደረገው አኮር ሆቴልስ በአዲስ አበባ ሶስት ሆቴሎችን ለመክፈት የሚያስችለውን የውል ስምምነት ማድረጉን አስታወቀ፡፡

መርኪዩር፣ ኢቢስ ስታይል እና ኢቢስ የተባሉ ሆቴሎችን፥ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች እንደሚገነባ ድርጅቱ ገልጿል፡፡

መርኪዩር ሆቴል 162 የመኝታ ክፍሎች ሲኖሩት፥ በፈረንጆቹ 2020 ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ተነግሯል፡፡

ኢቢስ ስታይልስ ደግሞ 135 የመኝታ ክፍሎች እና ሙሉ የሆቴል አገልግሎቶችን በመያዝ በ2019 እንደሚጠናቀቅ ተጠቁሟል፡፡

ሶስተኛው የአኮር ሆቴልስ አካል የሆነው ኢቢስ ሆቴል ደግሞ ባለ 22 ወለል ህንጻ ሲሆን 230 የመኝታ ክፍሎች ይኖሩታል፡፡

ሆቴሉ በ2021 የፈረንጆች ዓመት እንደሚጠናቀቅ ነው የተገለጸው፡፡

የሆቴሎቹ ግንባታ በአፍሪካ ህብረት እና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ አቅራቢያ እንደሚገነቡ በውል ስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ የጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ኩባንያው በአዲስ አበባ ሆቴሎችን ለመክፈት እንዲያስብ አድርገውታል ነው የተባለው፡፡

የድርጅቱ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ዋና ስራ አስፈጻሚ ስቴቨን ዴንስ፥ የሶስቱ ሆቴሎች የግንባታ ውል የአኮር ሆቴልስን ተደራሽነት እንደሚያሰፋው ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚገነቡት ሆቴሎች ጥሩ አገልግሎትን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን ይቀላቀላሉም ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው፡፡

አኮር ሆቴልስ በአፍሪካ በርካታ ሆቴሎች ያሉት ሲሆን፥ ከ10 ሺህ በላይ ሰራተኞች በእነዚህ ሆቴሎች እንደሚሰሩ ተነግሯል፡፡

 


ምንጭ፡-http://www.bizcommunity.com/ እና http://www.reuters.com/