የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር በዘርፉ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠር እየተንቀሳቀስኩ ነው አለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር በግንባታ ዘርፉ የስራ እድል ለመፍጠር በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገለጸ፡፡

ማህበሩ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል ዛሬ በአዲስ አበባ እያከበረ ነው፡፡

ማህበሩ እስካሁን ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር የቻለ መሆኑንና በሂደቱ የጥራት የዲዛይንና የአቅም ማነስ ችግር ፈተና እንደሆኑበት ጠቁሟል።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ከቴክኒክ እና መያ ስልጠና ተቋማት ተመርቀው ለሚወጡ ወጣቶች የስራ እድል እየተፈጠረ ነው ብሏል፡፡

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ኢንጅነር አበራ በቀለ እንደተናገሩት፥ በማህበሩ ውስጥ ያሉ ተቋራጮች በርካታ የግንባታ ስራዎችን እያከናወኑ ነው፡፡

ይህም በሀገሪቱ የግንባታ ሂደት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ሲሆን፥ በተለይም የግንባታ ዘርፍ ብዙ የሰው ኃይል የሚፈልግ በመሆኑ የስራ እድሎች እየተፈጠሩ ጠቅሰዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የምህንድስና ተማሪዎችም ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ፥ በግንባታው ዘርፍ እንዴት መስራት እንዳለባቸው በሚያሳይ መልኩ የተግባር ልምድ እየወሰዱ ነው ብለዋል፡፡

ማህበሩ የግንባታ ተቋራጮች የአቅም ግንባታ እንዲያገኙ በማድረግ፥ በግንባታ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየሰራ ነው፡፡

በተቋራጮቹ በኩል የሚታዩትን ችግሮች በተለይም፥ ግንባታዎችን በተያዘላቸው በጀት፣ የጊዜ ገደብ እና ጥራት አለማጠናቀቅን ለመፍታት ከመንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ኢንጅነር አበራ አንስተዋል፡፡

በማህበሩ ውስጥ ያሉት ከ1 ሺህ 600 በላይ ተቋራጮችም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የስራ ላይ ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችል አሰራር ለመዘርጋትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራሁ ነው ብሏል ማህበሩ፡፡

ከተደራሽነትም አንጻር ማህበሩ በሀዋሳ፣ በባህርዳር እና በመቀሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አሉት፡፡

 

 


በዳዊት በጋሻው