የሀዋሳ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አገልግሎት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን የኢንዱስትሪ ፓርኩን ተከትሎ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት የጉምሩክ አገልግሎት ስነ ስርዓት መጀመሩን ገልጿል።

የጉምሩክ ስነ ስርዓቱ በሀዋሳ መጀመሩ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ባሻገር በደቡብ ክልል እና አከባቢዋ የሚገኙ ባለሃብቶች

አገልግሎቱን ለማግኘት ቀድሞ ወደ አዳማ እና ሞጆ በመሄድ የሚያወጡትን ወጪ ይቀንስላቸዋል ተብሏል።

የሀዋሳ የጉምሩክ ስነ ስርአት የስራ ሂደት አስተባባሪ ተወካይ አቶ ደረጀ ወልደሚካኤል እንዳሉት፥ የጉምሩክ አገልግሎቱ ከኢንዱስትሪ ፓርኩ ባሻገር በክልሉ በኢንቨስተመንት ለተሰማሩ ባለሃብቶች አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

በከተማዋ የጉምሩክ አገልግሎቱ መጀመር ለኢንቨስትመንት እቃዎች ደህንነትም ትልቅ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ አስመጪዎችን ቁጥር ለማብዛት እና ለማሰባጠር በንግድ እቃዎችም ላይ የጉምሩክ ስነ ስርአት ለመጀመር መታቀዱን ተናግረዋል።

የጉምሩክ ስነ ስርአቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ማምረት ስራ ገብቶ እቃዎችን ወደ ውጭ መላክ ሲጀምር ተገቢውን የጉምሩክ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ብለዋል አቶ ደረጀ።

 በአሳየናቸው ክፍሌ