የአዳማ ከተማ ገቢዎች ፅህፈት ቤት ከ 331 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዳማ ከተማ ገቢዎች ፅህፈት ቤት በ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ውስጥ ከ 331 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል።

ከተሰበሰበው ገቢ ከ240 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከመደበኛው የተገኘ ሲሆን፥ ከ110 ሚሊየን ብር በላይ የሚሆነው ደግሞ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት እንደተገኘ፥ የፅህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ ኢዮብ ያእቆብ ለፋናብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

ፅህፈት ቤቱ በአምስት ወራት ውስጥ ከ319 ሚሊየን ብር በላይ ከመደበኛ፤ ከ130 ሚሊየን ብር በላይ ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ለመሰብሰብ አቅዶ እንደነበር ነው ሃላፊው የተናገሩት፡፡

ሆኖም በአምስት ወራት ውስጥ የተገኘው ገቢ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር የመደበኛው ገቢ ከተያዘው እቅድ 75 ነጥብ 39 በመቶ፥ ከማዘጋጃ የተገኘው ገቢ ደግሞ የእቅዱን 85 ነጥብ 09 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ማሳካት መቻሉንም አቶ ኢዮብ ገልፀዋል።

ለእቅዱ አለመሳካት ተከስቶ የነበረውን ሁከት ተከትሎ ስራዎችን በተገቢው መንገድ ማከናወን ባለመቻሉ እና ከደረሰኝ አጠቃቀም ጉድለት ጋር የተያያዙ ክፍተቶች እንደ ችግር የተወሰዱ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በዓመቱ መጨረሻም የተያዘውን እቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኢዮብ፥ በበጀት ዓመቱ ከመደበኛው እና ከከተማው ማዘጋጃ ቤት ከ964 ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል።

 

 

በዙፋን ካሳሁን