የስጦታ እቃዎች ገበያ ሞቅ ደመቅ ብሎ ሰንብቷል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 28፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገና በዓልን አስመልክቶ የስጦታ እቃዎች ገበያ ሞቅ ደመቅ ብሎ ሰንብቷል።

የገና በዓል የስጦታ ገበያ ከሌሎች በት የተለየ ድምቀት እንዳለውም ያነጋገርናቸው የስጦታ እቃ መሸጫ ባለሱቆች ነግረውናል።

በተለየ መልኩ የገና በዓል መለያ የተደረጉ በቀይ እና ነጭ ቀለሞች ያሸበረቁ ስጦታዎችም በየመሸጫ ሱቆች ጎልተው ይታያሉ።

በእነዚህ ቀለማት ያሸበረኩ አሻንጉሊቶች፣ ኮፍያዎችና ሌሎች ምርቶችም ከስጦታ እቃዎቹ መካከል ይገኙበታል።

ከበአሉ ጋር በተያያዘ ለማድመቂያነት የሚውሉ የማስጌጫ እቃዎች ባለቀለም ሻማዎች፣ አበቦች፣ ፖስት ካርዶች እና ቼኮሌቶች ብዙ ገዥ አላቸው።

ከሁሉም የስጦታ እቃዎች በበለጠ ግን ሰዎች ፖስት ካርዶችን በብዛት እንደሚገዙ ነው ፋና ብሮድካስቲንገ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ነጋዴዎች የገለጹት።

በጎዳና ላይ ካርዶቹን እንደ አይነቱ ዣንጥላ ላይ ዘርግተው የሚሸጡትም የተሻለ ገበያ ነበራቸው።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ መልክ እየተሰሩ የመጡት ባህላዊ ይዘት ያላቸው ፖስት ካርዶች የተሻለ ተፈላጊነትን ማግኘታቸውንም ሻጮቹ ነግረውናል።

ከስጦታ መሸጫ ሱቆች ባሻገርም የዶሮ፣ የእንቁላል፣ የሽንኩርት፣ የበግ እና የበሬ ገበያዎችም ሰሞኑን ደመቅ ብለው ሰንብተዋል።

በሾላ ገበያ ዶሮ ከ120 ብር ጀምሮ እንቁላል ደግሞ በሶስት ብር ከሃያ ሳንቲም ሲሰጭ ተመልክተናል።

በግም እንደ አይነቱ ከ800 ብር ጀምሮ፣ ሰንጋ በሬ ደግሞ ከ10 ሺህ ብር ጀምሮ እየተሸጠ መሆኑን ሸማቾች ገልጸዋል።

 

 

በትዕግስት አብርሃም