ኬንያ የ2018 የቻን የእግር ኳስ ውድድር አስተናጋጅነቷን ተነጠቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ካፍ ኬንያ የ2018 የቻን የእግር ኳስ ውድድርን ማዘጋጀት አትችለም በማለት የአስተናጋጅነት መብቷን ነጥቋታል።

ሀገር ውስጥ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የ2018 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) በኬንያ አስተናጋጅነት ነበር የሚካሄደው።

ሆኖም ግን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጋና አክራ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባው የኬኒያን የአስተናጋጅነት መብት ነጥቋል።

ውሳኔውም በካፍ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ የተመራ አስቸኳይ ስብሰባ ከተካሄደ አንድ ቀን በኋላ ነው ይፋ የተደረገው።

እንደ ካፍ ገለጻ፥ ውሳኔው ላይ የተደረሰው በሀገሪቱ በተደረገ ፍተሻ ከዝግጅት ጋር ተያይዞ መዘግየቶች በመኖራቸው ነው።

የካፍ አጣሪ ቡድን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከመስከረም 1 እስከ መስከረም 17 2017 በኬኒያ ባካሄደው ምርመራ ውድድሩን ለማስተናገድ ከሚያስፈልጉ ስታዲየሞች እስካሁን ዝግጁ መሆኑን የቻለው አንድ ብቻ መሆኑንም አስታውቋል።

የኬኒያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ኤፍ.ኬ.ኤፍ)፥ የቻን የአፍሪካ ዋንጫ በተሳካ መልኩ ማዘጋጀትን ለኬንያውያን እና ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እውን ለማድረግ እየሰራ እንደበረ አስታውቋል።

ከስፖርት መሰረተ ልማት በተጨማሪም የኬኒያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት መሰረዙን ተከትሎ በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ እንዳሳሰባቸውም የተወሰኑ የካፍ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በዚህ የተነሳም ኬኒያ የ2018 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) አዘጋጅነቷን ተነጥቃለች ነው የተባለው።

ኬኒያ ከዚህ ቀደምም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1996 የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅነት መነጠቋ ይታወሳል።

በወቅቱም የአፍሪካ ዋንጫውን የማስተናገድ እድል ለደቡብ አፍሪካ ነበር ተላልፎ የተሰጠው።

የ2018 የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ኬኒያን በመተካት የሚያስተናግደውን ሀገር አወዳድሮ የመምረጥ ስራ በአስቸኳይ እንደሚካሄድም ካፍ አስታውቋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከጥር 4 እስከ 27 2018 የሚካሄደው የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ውድድር ላይ 16 ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፥ በውድድሩ ላይም ሀገር ውስጥ ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው የሚካፈሉት።

በተያያዘ ካፍ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤው ካሜሮን የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነቷ ለጊዜው ባለበት ይቀጥላል ብሏል።

ሆኖም ግን የካፍ አጠጣሪ ቡድን ወደ ስፍራው በመጓዝ ምርመራዎችን ካካሄደ በኋላ ካሜሮን በአስተናጋጅነቷ ትቀጥል ወይስ ትነጠቅ የሚለው ላይ ውሳኔ አንደሚሰጥም ካፍ አስታውቋል።

ካፍ የ2019 ከ23 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነትምን ከዛምቢያ በመንጠቅ ለገብፅ አሳልፎ መስጠቱን ገልጿል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ