የህንዱ ፓትርያርክ ቅዱስ ባስልዮስ የመስቀልን በዓል ለማክበር አዲስ አበባ ይገባሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ቅዱስ ባስልዮስ በመስቀል ደመራ በዓል ላይ ለመገኘት፣ ነገ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ገለፀች።

ፓትርያርኩ በበዓሉ ለመታደም የሚመጡት በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ፓትርያክር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮ¬ጵያ ግብዣ ነው።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ማር ቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፤ ከፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጋራ ተገናኝተው እንደሚነጋገሩም ይጠበቃል።

በቤተ ክርስትያኒቷ የትንሳዔ ዘጉባዔ ማተሚያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ንቡረ ዕድ ኤሊያስ አብርሃ እንደገለጹት፥ ፓትርያርኩ የሕንድ ቤተ ክርስትያንን ጨምሮ 50 ልዑካንን በመምራት በኢትዮጵያ የአራት ቀናት ጉብኝት ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ኃላፊዎችና የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምዕመናን አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው ገልጸዋል።

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጋር በመሆን በመስቀል አደባባይ በመገኘት የደመራን በዓል ያከብራሉ።

አቡነ ማትያስ፣ ባለፈው ዓመት ህንድን በጎበኙበት ወቅት ባቀረቡላቸው ግብዣ፣ የዘንድሮውን የመስቀል በዓል በኢትዮጵያ የሚያከብሩት ቅዱስ ባስልዮስ ማር ቶማ ጳውሎስ ዳግማዊ፣ በ2005 ዓ.ም የ6ኛው ፓትርያርክ በዓለ ሲመት ለመገኘት ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን የአሁኑ ጉብኝታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ምንጭ፦ ኢዜአ