ዋልያዎቹ ከዩጋንዳ አቻቸው ጋር በመጪው ቅዳሜ የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከኬኒያ፣ ጋና እና ሴራሊዮን ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ መያዙ ይታወሳል፡፡

ብሔራዊ ቡድኑ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የወዳጅነት ጨዋታውን በመጪው ቅዳሜ በሀዋሳ ስታዲየም እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ስታዲየም እንደሚደረግ ሲጠበቅ የነበረው ጨዋታ ወደ ሃዋሳ ስታዲየም የተዛወረው የአዲስ አበባ ስታዲየም በዝናብ ስለተጎዳ መሆኑንም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።

25 ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ በመጥራት ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አዲስ አበባ የሚያደርገውን ልምምድ ዛሬ ጨርሶ ነገ ወደ ሀዋሳ ያቀናል፡፡

ከግብጽ ሊግ ቡድኑን የተቀላቀሉት ኡመድ ኡኩሪና ሽመልስ በቀለ ከቀናት እረፍት በኋላ ዛሬ ከቡድኑ ጋር የመጀመሪያ ልምምዳቸውን እንደሚያደርጉ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በኩል ምንም አይነት የተጨዋች ጉዳት እንደሌለ ተነግሯል፡፡

በ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የነበረውና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የሚገኘው የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን፥ በቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰር ቦቢ ሚቾ እየተመራ ወደ አትዮጵያ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

የቅዳሜው ጨዋታ ለአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡

 

 

 

 

 


በኢዮኤል ዘርይሁን