ነገ ለሚጀመረው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ከነገ ጀምሮ ለሚሰጠው የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በቂ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ።

የ2009 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አጠቃላይ የትምህርት ማጠናቀቂያና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብቃት መመዘኛ ፈተናዎች ከነገ ግንቦት 23 ቀን እስከ ሰኔ 1 ቀን 2009 ዓ.ም ይሰጣል።

የ10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ከነገ ጀምሮ እስከ ፊታችን ዓርብ ድረስ ሲሰጥ፥ የ12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ደግሞ ከቀጣዩ ሰኞ እስከ ሃሙስ ድረስ የሚሰጥ ይሆናል።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲም ለፈተናው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጠቅሶ፥ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን ከኩረጃ ነጻ በሆነ መልኩ ሊያካሂዱ እንደሚገባ አሳስቧል።

በነገው የ10ኛ ክፍል የሁለተኛ ደረጃ ማጠናቀቂያ ፈተና፥ 1 ሚሊየን 206 ሺህ 869 ተማሪወች ለፈተና ይቀመጣሉ።

ከዚህ ውስጥ 564 ሺህ 40ዎቹ ሴቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ደግሞ ወንዶች ናቸው።

ከ72 ሺህ በላይ ባለሙያዎችም ለዚህ ፈተና ዝግጁ ሆነዋል ነው የተባለው።

በመላ ሃገሪቱ ለሚሰጠው ፈተናም 3 ሺህ 500 ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውንም ኤጀንሲው አስታውቋል።