ጎግል የማፈላለጊያ ገጹ ላይ “ፐርሰናል” የተባለ አዲስ አገልግሎት አቀረበ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2009(ኤፍ.ቢ.ሲ) መረጃዎችን ለማፈላለግ በርካቶች የሚጠቀሙበት ጎግል አሁን ደግሞ ሰዎች አብዛኛው ሰዓታቸውን ከጎግል ጋር እንዲያሳልፉ የሚያደርግ ማሻሻያ ይዞ መጥቷል እየተባለ ነው።

ጎግል በማፈላለጊያ ድረ ገጹ ላይ “ፐርሰናል (personal)” የተባለ አዲስ አገልግሎት ይዞ መቅረቡ ነው የተነገረው።

“ፐርሰናል” የተባለው አዲሱ አገልግሎት በጎግል ላይ መረጃ በምንፈላልግበት ጊዜ የምንፈልገውን ይዘት ብቻ ለይተን እንድናወጣ የሚያስችለን ተብሏል።

የጎግል ፐርሰናል አገልግሎትን ማግኘት የምንችለው ወደ ጎግል አድራኛችን ስንገባ ብቻ ነው የተባለ ሲሆን፥ የምናፈላልገው ነገር ውጤትም ከሌሎች የጎግል አገልግሎቶች ማለትም እንደ ጂ ሜይል እና ጎግል ፎቶዎች ካሉት ላይ በማሰባሰብ ያቀርብልናል።

በማፈላለጊያችን ውስጥ ለምሳሌ “አዲስ አበባ” በማለት በምናስገባበት ጊዜ ጎግል ከአዲስ አበባ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን መስፈንጠሪያዎች (ሊንኮችን) በመደበኛነት ያመጣልናል።

ከዚህ በተጨማሪም ከሚመጡት ዝርዝር ከፍ ብሎ ዜና፣ ምስል፣ ቪዲዮ እና ሌሎች አማራጮችን ያመጣልናል።

ከሚዘረዘሩት አማራጮች ውስጥም “ሞር (more)” የሚለው ውስጥ በመግባት “ፐርሰናል (personal)” የሚለውን አማራጭ ማግኘት እንችላለን።

ፐርሰናል የሚለውን በምንጫንበት ጊዜም ከጎግል ማፈላለጊያ ጋር ተመሳሳይ ወደ ሆነ ገፅ የሚወስደን ይሆናል።

በዚህም የምንፈልገው ነገር አዲስ አበባ ከሆነ በአጀንዳችን ላይ ከአዲስ አበባ ጋር ተያያዠነት ያላቸውን ዝርዝሮች፣ አዲስ አበባ የሚል ቃል የያዙ በጂ ሜይል የተላኩልን መልእክቶችን በዝርዝር ያስቀምጥልናል።

Google_Personal_2.png

የሚመጣልንን ውጤትም እኛ ብቻ የምናየው መሆኑም ተነግሯል።

“ፐርሰናል” የተባለው አዲሱ የጎግል ማፈላለጊያ አገልግሎት በአሁኑ ጊዜ ለሁሉም ተጠቃሚዎቹ ያልቀረበ ሲሆን፥ በሂደት ግን ሁሉም ጋር መድረስ እንደሚጀምር ከኩባንያው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ምንጭ፦ www.independent.co.uk