በልጅነት የሚከሰተውን የስኳር በሽታን ከጅምሩ የምናስቆምበት መንገድ አግኝተናል- ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተመራማሪዎች ከልጅነት አንስቶ የሚከሰተውን አይነት 1 የስኳር በሽታ ከጅምሩ ማስቆም የሚቻልበትን መንገድ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።

ይህም በዱቄት መልክት በተዘጋጀ ኢንሱሊን አማካኝነት የህፃናትን የበሽታ መከላከል ስርዓት በሽታውን እድሜ ልካቸውን እንዲከላከል በማለማመድ እንደሆነም ገልፀዋል።

ኢንሱሊን በደማችን ውስጥ ያለን የስኳር መጠን የሚቆጣጠር ሆርሞን ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅትም የስኳር በሽታን ለማከም በመድሃኒትነት ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ የሚውል ነው።

ተመራማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ሙከራ ለማድረግ እየተዘጋጁ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በብሪታንያ የሚገኙ እና የእርግዝና ክትትል በማድረግ ላይ የሚገኙ ፍቃደኛ ነብሰ ጡር እናቶች ለሙከራው እንዲመዘገቡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በጥናቱ ላይ የሚካፈሉ ወላጆችም ለህፃናት የተዘጋጀውን የኢንሱሊን ዱቄት ህጻናት ልጆቻቸው ከ6 ወር ጀምሮ እስከ 3 ዓመታቸው በየቀኑ እንዲሰጧቸው ይደረጋል።

በዚህ ወቅትም ከምርምር ማእከሉ የህፃናቱን የጤንነት ሁኔታ የሚከታተል ቡድን በየጊዜው ህፃናቱን የሚጎበኝ መሆኑም ተነግሯል።

በጥናቱ ወቅትም ከጥናቱ ተሳታፊዎች ግማሹ ትክክለኛውን ኢንሱሊን ለልጆቻቸው እንዲጡ ይደረጋል የተባለ ሲሆን፥ ግማሹ ደግሞ ምንም መድሃኒትነት የሌለው ዱቄት እንዲወስዱ ይደረጋል ተብሏል።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በዚህ መልኩ 30 ሺህ ህፃናት ላይ ጥናቱን ለማካሄድ መዘጋጀቱንም ነው ያስታወቀው።

የኢንሱሊን ዱቄትን ለህፃናት በማንኪያ በመመገብ ብቻ ከአይነት አንድ የስኳር በመመገብ የበሽታ መከላከል ስርዓታቸው አይነት አንድ የስኳር በሽታን መከላከል እንዲለምድ ማስቻል ይቻላል የሚለው ላይም ሙሉ እምነት እንዳላቸው ነው ተመራማሪዎቹ የሚናገሩት።

በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ከ1 ሺህ ህፃናት ውስጥ 1 ህፃን በአይነት አንድ የስኳር በሽታ የተጠቀቃ ሲሆን፥ አይነት አንድ የሚባለውን የስኳር በሽታን መከላከያ መንገድም እስካሁን አልተገኘለትም።

ተመራማሪዎች አሁን አግኝተናል የሚሉት መንገድ ስኬታማ ከሆነም በሽታውን ቀድሞ ለመከላከል ያስችላል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል።

ምንጭ፦ www.bbc.com