ካራቫት ማሰር ወደ አእምሮ በሚገባው የደም ዝውውርና በስራ ውጤታማነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት…

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአብዛኛው የስራ ገበታ ላይ ወንዶች በሚከተሉት የአለባበስ ደንብ (ፕሮቶኮል) ውስጥ ካራቫት ማሰር የግድ ነው።

ሆኖም ግን በቅርቡ የወጣ አዲስ ጥናት ከራቫትን አዘውትሮ ማሰር የደም ቧንቧዎችን በማጥበብ ወደ አእምሯችን የሚገባውን የደም ዝውውርን እንደሚያስተጓጉል አስታውቋል።

ይህ ደግሞ አእምሯችን የተሰጠውን ስራ በአግባቡ እንዳይከውን በማድረግ፤ በስራችን ላይ ውጤታማ እንዳንሆን ያደርጋል ነው ያለው ጥናቱ።

ጥናቱ በጀርመን ውስጥ በሚኖሩ 30 ወንዶች ላይ የተካሄደ ሲሆን፥ በጥናቱ ላይ የተካፈሉ ወንዶችም ከራቫት በማሰር በኤም.አር.አይ መሳሪያ የደም ዝውውራቸው ታይቷል።

በዚህም ካራቫት ያሰሩ ወንዶች ወደ አእምሯቸው የሚገባው የደም ዝውውር መጠን በ7 ነጥብ 5 በመቶ ቀንሶ መታየቱን ነው ጥናቱ ያመለከተው።

ወደ አእምሯችን የሚገባው የደም ዝውውር ሲገታ ደግሞ አእምሯችን ስራውን በአግባቡ መከወን እንደሚሳነውም ጥናቱን ያካሄዱት ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

የጥናቱ ውጤትም በቴክኖሎጂው ዘረፍ ውጤታማ የሆኑት የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ እና የአፕል ባለቤት የነበሩት ስቲቭ ጆብስ ያለከራቫት የሚለብሱትን አለባበስ የሚያበረታታ መሆኑም ተነግሯል።

ties_22.png

የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ እና የአፕል ባለቤት የነበሩት ስቲቭ ጆብስ ሙሉ ሱፍ ከነካራቫት ከመልበስ ትልቅ ካናቴራ (ቲ ሸርት) ለብሰው ነው የሚስተዋሉት።

ከዚህ ቀደም የተሰራ አንድ ጥናትም ካራቫት ማሰር በአይን ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ያመላከተ ሲሆን፥ በጥናቱም ካራቫት አዘውትሩ ማሰር በአሳሪው ግለሰብ አይን ላይ ጫና ይፈጥላል ተብሏል።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk