ሙቅ ውሃ መጠጣት የሚያስገኛቸው የጤና ጥቅሞች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010(ኤፍ.ቢ.ሲ) በየቀኑ ሙቅ ውሃ መጠጣት ጤናን በማሻሻል ያለው ጥቅም የላቀ መሆኑን ተመራማሪዎች ገልፀዋል።

በቂ ንፁህ ውሃ መጠጣት ለቆዳ፣ ለጡንቻ እና ለመገጣጠሚያ ክፍሎች ጤንነት ያለው ጥቅም የላቀ ነው።

ውኃ የሰውነት ሕዋሳት ንጥረ ነገሮችን እንዲመገቡ እና በሽታን እንዲከላከሉም ይረዳቸዋል።

ሙቅ ውሃ መጠጣት ደግሞ ጤናን ለማሻሻል የሚረዳ ቀላል ዘዴ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ ከሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች መካከል፦

1. ምግብ በሆዳችን ውስጥ ቶሎ እንደዲዋሃድ

አንድ ሰው በቂ ውሃ ካልጠጣ ትንሹ አንጀት በምግብ እና በመጠጥ የሚወስደውን ፈሳሽ መጠቀምን ይመርጣል።

ይህ ደግሞ የሰውነት ፈሳሽ ድርቀት ህመም በማስከተል የሆድ ድርቀት እና የሽንት ችግር ሊያመጣ ይችላል።

ከዚህ ባለፈ ሌሎች ከባድ ችግሮችን ማለትም ኪንታሮትን እና የሆድ በሽታን ያመጣል።

ውሃን አሙቆ መጠቀም ደግሞ እነዚህን ችግሮች ከመከላከል በተጨማሪ የሆድ ድርቀትን ይቀንሳል ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ።

2. መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት ለማስወገድ

ጥናቶች ሙቅ ውሃ መጠጣት መርዛማ ነገሮችን ከሰውነታችን እንዲወገዱ ያግዛል ሲሉ ይገልፃሉ።

ለዚህም አንድ ሰው በሚገባ የሞቀ ውሃ በሚጠጣበት ጊዜ የሰውነቱን ሙቀት መጠን በመጨመር ላብ ሊያወጣ ይችላል።

ላቡም መርዛማ ነገሮችን ለማስወገድ እና እጢዎቹን ለማፅዳት ያግዘዋል ማለት ነው።

3. የተሻለ የደም ዝውውር እንዲኖር

የሞቀ ውሃ መጠጣት የደም ቧንቧን ወይም ሥሮችን በማስፋት የደም ዝውውርን ያሻሽላል።

ይህ ደግሞ ጡንቻዎች እንደፈለጉት እንዲንቀሳቀሱ እና ህመምን ለመቀነስ ይረዳቸዋል፤ ብሎም የተሻለ የደም ዝውውር እንዲኖር ይረዳል ነው የተባለው።

4. የሰውነት ክብደት ለመቀነስ

ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ሁል ጊዜ ውሃን መጠጣት አንድ ሰው ክብደቱን እንዲቀንስ ይረዳዋል።

በተጨማሪ በሰውነታችን ውስጥ ያለውን ቆሻሻ በማስወገድ ጥሩ ስሜት እንዲኖረን፣ ሰውነታችን ንጥረ ነገሮችን እንዲመገብ እና ውፍረት እንዲቀንስ ይረዳል ተብሏል።

ተመራማሪዎቹ ሰዎች ምግብ ከመመገባቸው በፊት 500 ሚሊ ሊትር ውኃ ቢጠጡ፥ የተመገቡት ምግብ የመፈጨት ፍጥነቱ 30 በመቶ ሊጨምር እንደሚችልም አመልክተዋል።

98 ነጥብ 6 ዲግሪ ሙቀት ያለው ውሃ ሲሆን ደግሞ ምግብ የመፈጨት ፍጥነቱ 40 በመቶው ይጨምራል።

ይህ የምግብ የመፈጨት ሂደትም ከ30 እስከ 40 ደቂቃዎች የሚቆይ ነው የሚሆነው።

5. የህመም ስሜት ይቀንሳል

ሙቅ ውሃ መጠጣት በተለይ ለተጎዱ ጡንቻዎች የደም ዝውውርን እና ፍሰትን ያሻሽላል፤ ይህ ማለት ግን ህመም ያስቆማል ማለት አይደለም።

ይሁን እንጂ ሰዎች ህመምን ለመቀነስ በየቀኑ የሞቀ ውሃ ፓኬቶችን እና ጠርሙሶችን ከተጠቀሙ የህመም ስሜታቸው ሊቀንስ እንደሚችል ጥናቶች አረጋግጠዋል።

በተጨማሪም ውኃ አሙቆ መጠቀም አንዳንድ የውስጥ ህመም ማስታገሻ ሊሰጥ ይችላል፤ ሆኖም ሙቀት እብጠት ካለ ግን ሊያባብሰው እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው ሲሉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

6. ጉንፋንን በመዋጋት የአፍንጫ ጤንነትን ያሻሽላል

ሙቅ ውሃ መጠጣት በጉንፋን እና አለርጂ ምክንያት በአፍንጫ አከባቢ የሚፈጠረውን የአፍንጫ መቆጣት ጫና ለመቀነስ ይረዳል።

በውሃ እንፋሎት መታጠንም በአፍንጫ አከባቢ ያለውን ቁስለት ቶሎ እንዲደርቅ ሊያግዝ ይችላል።

ሙቅ ውሃ መጠጣት ንፍጥ በፍጥነት እንዲጓዝ ስለሚያደርግ ሳል ቶሎ እንዲተወን ይረዳል ተብሏል።

7. ሙቅ ውሃ ከቡና ወይም ከሻይ ጋር ቀላቅሎ በመጠቀም ህመምን መከላከል

ሙቅ ውሃ ከቡና ወይም ከሻይ ጋር ቀላቅሎ መጠቀም የሰውነት ድርቀትን ከማስወገድ ባሻገር ተጨማሪ የጤና ጥቅሞች ይሰጣል።

በአውሮፓውያኑ 2017 የወጡት ጥናቶች እንደሚያመላክለቱት ቡና መጠጣት ካንሰር፣ የስኳር በሽታ፣ ጉበት እና የልብ ህመም አደጋን በመከላከል እድሜን ያራዝማል።

ሻይ ደግሞ የልብ ሕመም፣ የስኳር በሽታ እና የጉበት በሽታን ሊከላከል ይችላል።

8. ጭንቀትን ለመቀነስ

የሞቀ ውሃ መጠቀም የአእምሮ ጭንቀት እና ውጥረት ይከላከላልም ተብሏል።

የሞቀው ውሃ ሳይቀዘቅዝ መጠቀም እጅ፣ ምላስ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ሊያቃጥል ስለሚችል በተቻለ መጠን የሞቀውን በመጠኑ አቀዝቅዞ መጠቀም ይመከራል።

የቡና ሙቀት ደግሞ በ136 ዲግሪ ፋራናይት (57 ነጥብ 8 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ) ቢሆን ይመረጣል ሲሉ ባለ ሙያዎች ይመክራሉ።

ምንጭ፦ medicalnewstoday.com