በዓለም ላይ ያሉ እናቶች ጨቅላ ልጆቻቸውን በሙዚቃዊ ቃና የሚያባብሉበት ምክንያትና ፋይዳ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 3፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በመላው ዓለም የሚገኙ እናቶች ጨቅላ ልጆቻቸውን በሚያጫውቱበት ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ በውስጣዊ ግፊት ድምፃቸውን ወደ ሙዚቃዊ ቃና እንደሚቀይሩ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።

የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ በሰራው ጥናት እናቶች ህፃናቱን ለማባበል በሚያስቡበት ጊዜ አዕምሯቸው በከፊል የሚገነዘበውን ድርጊት እንደሚፈፅሙ ጠቅሷል።

በመላው ዓለም የሚገኙ እናቶች የቱንም ቋንቋ ቢናገሩ ጨቅላ ልጆቻቸውን በሚያባብሉበት ጊዜ ግን አንድ ዓይነት የማባበል ስልትን ይተገብራሉ ይላል ጥናቱ።

ከህፃናቱ ጋር ሲያወሩም ሆነ ሲጫወቱ ንግግራቸው ሙዚቃዊ መሆኑን ነው ጥናቱ ይፋ ያደረገው።

ይህ ዜማዊ የእናቶች ንግግር ደግሞ ጨቅላዎቹ በማባበል ሂደቱ እንዲሳቡ፣ የቋንቋ መልመድ አቅማቸው እንዲያድግ እና ቃላትን እና ዓረፍተነገሮችን በቀላሉ እንዲይዙ ያስችላቸዋል ብሏል።

የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እናቶች ከልጆች ጋር በሚያወሩበት ጊዜ የድኝምፃቸውን ቅላፄ የሚቀይሩበትን ልዩ መንገድ ደርስንበታል ነው ያሉት።

አንድ እናት ልጇን ከወለደችበት ጊዜ ጀምሮ በተለየ ቅላፄ ከልጇ ጋር የምታወራው እና የምታባብለው እናትነቷን ተገንዝብ እሷ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ጨቅላዎች እናታቸውን ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ እንዲያውቁ ያስችላቸዋል።

በዚህ ዙሪያ አባቶችም ልጃቸው አባትነታቸውን እንደያውቅ ለማድረግ የራሳቸውን የአነጋገር ስልት እንደሚጠቀሙ በተመሳሳይ አንስተዋል።

በጥናቱ እናቶች ከ7 እስከ 12 ወር እድሜ ያላቸውን ህፃን ልጆቻቸውን እና ሌሎች እድሜያቸው ከፍ ያሉ ልጆቻቸውን የሚያወሩበትን እና የሚያጫውቱበትን መንገድ በመመዝገብ ትንታኔ ቀርቧል።

በዚህ ትንታኔ መሰረት በመላው ዓለም ያሉ እናቶች ከጨቅላዎቹ ጋር ሲጫወቱ የድምፃቸውን ቅላፄ ሙዚቃዊ የሚያደርጉበት የጋራ ባህሪ መኖሩ ታውቋል።

ጀርመንኛ፣ ካንቶኒስ፣ ፈረንሳይኛ፣ እብራይስጥ፣ የሀንጋሪ ቋንቋ፣ መንደሪን፣ የሩሲያ ቋንቋ፣ ስፓኒሽኛን ጨምሮ 10 ቋንቋዎችን የሚናገሩ እናቶች ላይ ጥናቱ ተደርጓል።

በተሰራው ጥናትም ሁሉም እናቶች ጨቅላ ልጆቻቸውን በሚያባብሉበት ጊዜ ተመሳሳይ የድምፅ ለውጥ እንደሚያደርጉ ነው የተረጋገጠው።

በዊስኮንሲን ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና መምህሩ ፕሮፌሰር ጄኒ ሳፍሬይን ስለጥናቱ ግኝት ተጠይቀው እንደተናገሩት፥ እናቶች ከጨቅላዎች ጋር ሲጫወቱ ድምፃቸውን ከፍ እያደረጉ በዝግታ ይናገራሉ፤ አጫጭር ዓረፍተነገሮን ይጠቀማሉ።

ሆኖም እድመኔያቸው ከፍ ያሉ ልጆችን በሚያወሩበት ጊዜ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በፍጥነት እንዲሚያወሩ ይታወቃል ነው ያሉት።

በጉዳዩ ላይ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሰሩት ጥናትም መልካም ግምቶችን እንዳረጋገጠ ተናግረዋል።

የህፃናትን የቋንቋ ችሎታ እና የእናቶችን የድምፅ ለውጥን ሌሎች ተጨማሪ ጥናቶች ምካሄድ እንደሚገባቸው ነው የገለፁት።

 

 

 

 

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk