ህፃናት ለአዋቂዎች አርዓያ መሆን ይችላሉ-የስነልቦና ምሁራን

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ብዙዎቻችን በእድሜ የሚበልጡንን የቤተሰብ አባላት፣ ለስኬት የበቁ ሰዎችን አልያም የስራ ሃላፊያችንን የመልካም ኑሯችን ወይም የእድገት አርዓያ አድርገን ልናስብ እንችላለን።

ሆኖም ይህ እሳቤ አንዳንድ ጊዜ ውድቅ ሆኖ አዕምሯችን ባልገመትነው መልኩ አርዓያችንን ሊጠቁመን ይችላል።

ለአብነትም ህዓናት የታላላቆቻቸው ወይም የቤተሰቦቻቸው አርዓያ የሚሆኑበት ጊዜ አለ።

ግን ህፃናት በምን ምክንያት ወይም እንዴት ነው የታላለቆቻቸው አርዓያ ሊሆኑ የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የሚከተሉትን ነጥብች መመልከት ያስፈልጋል።

1. ህፃናት የሚፈልጉትን አልያም የተጠየቁትን ነገር በግልፅ የሚያደርጉ መሆናቸው

ህፃናት በአዕምሯቸው ውስጥ ያለን ሀሳብ፣ ፍላጎት ወይም ጥያቄ ለሰዎች በማጋራት በኩል አርዓያዎች ናቸው።

ምንልባትም ታላላቅ ሰዎች በይሉኝታ ምክንያት መናገር ወይመ መጠየቅ ያልፈለጉትን ሀሳብ ህፃናት በግልፅ በማውጣት ምሳሌ እንደሚሆኑ የስነልቦና ምሁራን ይናገራሉ።

ልጆች አንድን ነገር ሲጠየቁ ለማድረግ ወይም ምላሽ ለመስጠት አያወላውሉም።

በእድሜቸው ከልጅነት የወጡ ወይም ከወጣትነት እድሜ ጀምሮ ያሉ ሰዎች አንድን ነገር ለመናገር ሲፈልጉ ቃላትን በመምረጥ ብዙ ጊዜ ይጨነቃሉ።

ይህ ደግሞ ራስን በሳንሱር ውስጥ በማሳለፍ ሀቁን በቀጥታ በመናገር እና ባለመናገር ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋል።

ለዚህ ደግሞ የህፃናት ቀጥተኛ ተናጋሪነት በመልካም አርዓያ የሚወሰድ ነው።

2. በተፈጥሯቸው ሩህሩህ ናቸው

ህፃናት በተፈጥሯዊ አዕምሯቸው ውስጥ ብዙ መጥፎ ነገሮችን በማቆየት ወይም በመጨነቅ ጊዜ አያባክኑም።

በአምስቱም የስሜት ህዋሳታቸው ነገሮችን ቶሎ የመቀበል ችሎታ ያላቸው ሲሆን፥ ታላላቅ ሰዎች ቢያስቀይሟቸው ወይም ቢቆጧቸው ቂም አይዙም።

በትህትና እና በፍቅር በመቅረብ የሰዎችን ልብ ይገዛሉ።

ከዚህም በላይ አሁናዊ ህይወትን በመኖር በተለያየ ሀሳብ የሚወጠረው የታላላቆቻቸው አዕምሮ ከህፃናት መማር እንዳለበትም አርዓያ መሆን ይችላሉ።

3. የጨዋታን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ይረዳሉ

ህፃናት አዝናኝ እና አስደሳች የሆኑ ጨዋታዎች ወይም ቀልዶች ያላቸውን ፋይዳ በአግባቡ ይረዳሉ።

ለዚያም ነው ማንኛውም ሰው ቢያጫውታቸው፣ ተረት እንዲትርትላቸው፣ እንዲዘፍንላቸው አልያም ሌላ ቀልድ እንዲነግራቸው የሚፈልጉት።

ጨዋታውንም በአብሮ ተሳታፊነት ይታደማሉ።

በዚህም ፍፁም ደስተኛ እና ጤናማ አዕምሮን ያገኛሉ።

እድሜ እያደገ በሄደ ቁጥር ግን ሰዎች ጨዋታን ዋዛ እና ፈዛዛ ባስ ሲልም ምንም ዓይነት ጥቅም የሌለው አድርገው እንደሚወስዱት ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

ሆኖም ጨዋታ የአዕምሮን ስራ ለማቀላጠፍ፣ ጭንቀትን ለማስወገድ፣ ግንኙነትን ለማሻሻል እና የፈጠራ አቅምን ለመጨመር ጉልህ ፋይዳ አለው።

እነዚህን የጨዋታ እሴቶች እና ፋይዳዎች ቀድሞ በመረዳት እና ጥቅምን በማግኘት ህፃናት በእድሜ ለሚበልጧቸው ሰዎች አርዓያዎች ናቸው።

4. ፍፁም ራሳቸውን ሆነው ይገኛሉ

ህፃናት አንድ ስራ ትክክል ወይም ስህተት መሆኑ እስካልተነገራቸው ድረስ ሳያቋርጡ ሊያከናውኑ ይችላሉ።

ይህም የሚያሳየው ሰው ምን ይለኛል ብለው ሳይሆን ራሳቸውን ሆነው በመኖር እና ባለመጨነቅ ለታላላቅ ወንድም እና እህቶቻቸው ወይም ለወላጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

5. እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ በቀጥታ ይጠይቃሉ

ብዙ ጊዜ ማህበረሰቡ ራስን መቻል እና በራስ አቅም መንቀሳቀስን ያበረታታል።

በዚህም ምክንያት ችግር ቢያጋጥመን እንኳ ራሳችን ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን፤ ካልተሳካም ሁል ጊዜ ብቻችንን እንጨነቅበታለን።

በዚህ ጊዜ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ለአዕምሯችን ማሳመን በራሱ ድክመት ወይም ሽንፈት መስሎ ይታየናል።

ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ጎጂ በመሆኑ ድጋፍ ወይም እርዳታ በሚያስፈልግን ጊዜ፥ ቀጥተኛ በሆነ መንገድ መጠየቅ ያለብንን ሰው እንድንጠይቅ በማድረግ ረገድ ከህፃናት ብዙ መማር ይቻላል።

ህፃናት ሁሉንም ነገር በራሳቸው እንዲመልሱ የማይገደዱ ሲሆን ሌሎች ሰዎችም ይህንን ከህፃናቱ አይጠብቁም።

ህፃናቱ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ለመጠየቅ ወደ ኋላ ሳይሉ በቀጥተኛ መንገድ እንድናግዛቸው እና እንድንተባበራቸው ይጠይቁናል።

ከህፃናት ለመማር አዕምሯችንን ክፍት ካደረግነው እነሱ መልካም መምህሮች ናቸው ይላሉ የስነልቦና ምሁራን።

በአንድ ወቅት እኛ ማን እንደነበርን በማስታወስ የልጅነት መልካም ባህርያት በልቦናችን ውስጥ እንዲቀጥሉም ዘወትር በሚያከናውኗችው ድርጊቶች ያስተምራሉ።

“እኛ ልጆቻችን ስለህይወት ለማስተማር ስንሞክር፥ ልጆቻችን ህይወት ምን እንደሆነች ያስተምሩናል” የሚለው የቤት ለቤት የእናትነት መምህሯ አንጌላ ሺዊት አባባል ለህፃናት መልካም አርዓያነት ምሳሌ ይሆናል።

 

 

 

 

ምንጭ፦ሳይኮሎጂ ቱዴይ