በዓለም አቀፍ ደረጃ የህፃናትና የታዳጊዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው-ጥናት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፍ ደረጃ የህፃናት እና የታዳጊዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ

ባለፉት 40 ዓመታት የህፃናት እና ታዳጊዎች ከመጠን ያለፈ ውፍረት በ10 እጥፍ የጨመረ ሲሆን እንደ አዲስ ደግሞ 124 ሚሊየን ታዳጊ እና ህፃናት ለችግሩ ተጋልጠዋል።

በላንሴት የሰፈረው የጥናቱ ትንታኔ በ200 ሀገራት ላይ ያለውን የውፍረት ሁኔታ ዳሷል።

በዚህም በብሪታኒያ እድሜያቸው ከ5 እስከ 19 ዓመት ከሚሆናቸው 10 ህፃናት እና ታዳጊዎች መካከል አንዱ ለውፍረት የተጋለጠ ሆኖ ተገኝቷል።
በጣም ወፍራም ህፃናት ሲያድጉ በጣም ወፍራም ወጣት ስለሚሆኑ ለከፋ የጤና ችግር እንደሚያጋልጣቸው የጤና ባለሙያዎች ገልፀዋል።

የዓለም የውፍረት ቀን በሚከበርበት ዕለት ላንሴት ጥናታዊ ትንታኔውን ይፋ ያደረገው፥ የዓለም የውፍረት ፌደሬሽን ከመጠን በላይ ውፍረት የሚያመጣቸው የጤና ቀውሶች አሳሳቢ መሆኑን መግለፁን ተከትሎ ነው።

ፌደሬሽኑ ከ2025 ጀምሮ በየዓመቱ ከ920 ቢሊየን ፓውንድ በላይ ሊደርስ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በበለፀጉት የአውሮፓ ሀገራት የህጻናት የውፍረት ምጣኔ እየቀነሰ ቢሆንም፥ በሌሎች የዓለም አካባቢዎች ግን በአሳሳቢ ሁኔታ መስፋፋቱን የጥናቱ መሪና የለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ማጂድ ኤዛቲ ይናገራሉ።

ተመራማሪዎች ለህፃናት እና ለታዳጊዎች ከመጠን በላይ መወፈር ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ዋናው በቅናሽ ዋጋ የሚሸጡ እና ለውፍረት የሚዳርጉ ምግቦች ናቸው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የህፃናት እና የታዳጊዎች ውፍረት እየተስፋፋበት ከሚገኘው የዓለም ክፍል ውስጥ ግዙፉን ድርሻ የሚይዙት የምስራቅ እስያ ሀገራት ናቸው።

ቻይና እና ህንድ በዚህ ረገድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

ፖሊኔዥያ እና ማይክሮኔዥያ የሚባሉት ሀገራት ደግሞ ከህፃናት እና ታዳጊ ዜጎቻቸው ውስጥ ግማሽ ያህሉ ለውፍረት የተጋለጡ በመሆኑ ከፍተኛ የውፍረት ምጣኔ ላይ ተቀምጠዋል።

አሁን የዓለም ማህበረሰብ ለውፍረት የሰጠው ዝቅተኛ ግምት በዚህ ከቀጠለ ችግሩ የከፋ እንድሚሆን ነው ተመራማሪዎች የጠቆሙት።

በሌላ በኩል ከፈረንጆቹ 2000 ወዲህ ክብደታቸው ጤናማ ከሚባለው በታች የነበሩ ሴት እና ወንድ ልጆች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ ቁጥራቸው እየቀነሰ መጥቷል።

በ2016 ጤናማ ከሚባለው በታች ክብደት ያላቸው ታዳጊ እና ህፃናት ቁጥር 192 ሚሊየን ሆኗል።

ሆኖም በዓለም አቀፍ ደረጃ በ2016 ተጨማሪ 213 ሚሊየን ታዳጊዎች፥ ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት በመጋለጣቸው አስፈላጊ ስራዎችን ማከናወን ይገባል ተብሏል።

የምስራቅ እስያ፣ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት ህዝቦች ከጥቂት 10 ዓመታት ወዲህ ከጤናማ ውፍረት አልፈው ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት እየተጋለጡ ነው።

ዶክተር ሃሪ ሩተር የጥናቱ ተባባሪ ተመራማሪ ሲሆኑ፥ ከ10 ዓመት በፊት ቀጭን የነበሩ ሰዎች አሁን ክብደታቸው በጣም ጨምሮ ተገኝቷል ይላሉ።

በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ የመጣውን ከመጠን ያለፈ ውፍረት ለመግታት፥ ለውፍረት የሚዳርጉ አመጋገቦችን ማስተካከል እና ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ተገቢ ነው ተብሏል።

ከዚህ ውጭ ከ20 በላይ ሀገራት ከመጠን ያለፈ ውፍረትን ለመቀነስ ሲባል በጣፋጭ መጠጦች ላይ ታክስ እንዲቆረጥ ተግባራዊ አድርገዋል።

ዶክተር አሊሰን ቴድስተን በእንግሊዝ የህብረተሰብ ጤና ተቋም የስነምግብ ባለሙያ ናቸው፤ እርሳቸው እንደሚሉት የስኳር አጠቃቀም ቅነሳ መርሃ ግብርን ተግባራዊ በማድረግ የትውልዱን ጤናማነት ለማስተካከል ስራዎች ተጀምረዋል።

ህብረተሰቡን ማስገንዘብ፣ ማድረግ ያለበትን እና የሌለበትን ነገሮች ማሳወቅ ለተፈለገው ግብ መሳካት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ