አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ችግሮችን የሚቋቋሙባቸው 8 መንገዶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዩኒቨርሲቲ ገብቶ መማር ለወጣት ተማሪዎች አስደሳቹ የህይወት ክፍል ነው።

ሆኖም የሚያስጨንቁና የሚያስፈሩ ስነ ልቦናዊ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ።

በተለይም አዲስ አካባቢን ለመላመድ ከቤተሰብ ውጭ ርቆ ለመማርና አዲስ ጓደኞችን ለማፍራት የሚኖሩት በፍርሃትና በተስፋ የተሞሉ አዕምሯዊ ጉዳዮች ይጠቀሳሉ።

በአውሮፓ በተመስጦ ሙያ እውቅናን ያገኙት ዊል ዊሊያምስ፥ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ በቅድሚያ ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም ይላሉ።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ከብሪታኒያ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ሩብ ያህሉ ለአዕምሯዊ ችግሮች መዳረጋቸውንም አውስተዋል።

በተለይም ድብርትና ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት የተማሪዎቹ የጋራ ችግሮች ነበሩ ብለዋል።

ከቤተሰብ በመለየት ምክንያት የሚያጋጥሙ አዕምሯዊ ችግሮች ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ባወጡት መረጃ ከአዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል 35 በመቶዎቹ የቤተሰብ ናፍቆት በእጅጉ እንደሚፈታተናቸው ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት አንዳንዶቹ በትምህርታቸው ላይ አሉታዊ ጫና የሚፈጥር ድብርት እንዳጋጠማቸው ነው የተነገረው።

የተመስጦ ባለሙያው እንደሚሉት ከቤተሰብ ጋር በምቾት የኖሩበትን ህይወት ለቀው፥ ወደ አዲስ አካባቢ እና ማህበረሰብ መቀላቀል ፈታኝ እንደሚሆን ይታመናል ይላሉ።

ታዲያ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህን ፈታኝ ሁኔታ ተቋቁመው በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ደስተኛና ስኬታማ ቆይታ እንዲያደርጉ የሚከተሉትን መንገዶች ቢከተሉ ስንል አቅርበናቸዋል።

1. በዩኒቨርሲቲ ከአዳዲስ ጓደኞች ጋር ፈጥኖ ለመላመድ ጥረት ማድረግ

አዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሚከብዷቸው ነገሮች አንዱ እንደ ቤተሰብ የሚቀርቡት መልካም ጓደኛ ለማግኘት የሚያደርጉት ሂደት ነው።

በእርግጥ የሰው ልጅ ማህበራዊ አኗኗርን የሚከተል ፍጡር ቢሆንም፥ ስነ ልቦናዊ መራራቅ የሚፈጥራቸው መገለሎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ።

ይህ እንዳይሆን ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው ቤታቸው እንደሆነ በቅደሚያ ሊያስቡ ይገባል።

ከዚያም በአንድ የጋራ የተማሪዎች መኖሪያ ከተመደቡላቸው ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን፥ አዲሱን ህይወት እንደ ቤተሰባዊ ግንኙነት በማቅረብ መላመድ ያስፈልጋቸዋል።

ይህ ደግሞ ከቤተሰብ በመራቃቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን ፍፁማዊ የቤተሰብ ናፍቆት ቀለል ያደርግላቸዋል።

2. አዳዲስ ፈተናዎችን በራስ አቅም ለመጋፈጥ መወሰን

አዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ በክፍል ውስጥ የተሰጠን ጉዳይ በተማሪዎች እና በመምህራን ፊት አለማቅረብ፣ የተማሪዎች ህብረት ስብሰባ ሲኖር በተማሪዎች ፊት አስተያየትን ለመስጠት አለመድፈርን ጨምሮ በርካታ አዕምሯዊ ፍርሃት የታከለባቸው ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ።

የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚሉት ተማሪዎቹ በቅድሚያ ፍርሃት በውስጣቸው መኖሩን ማወቅ ይኖርባቸዋል።

ከዚያም የፍርሃቱ ምንጭ ምንድን ነው የሚለውን በራስ ሂደት ማወቅና መሰረተቢስ መሆኑን አምኖ በራስ ለመጋፈጥ መወሰን አለባቸው።

በተለይም የሚፈሩትና የሚጠሉትን ነገር በግዴታ ለማከናወን ቁርጠኛ አቋምን ወስደው መተግበር ይኖርባቸዋል ነው የሚሉት የስነ ልቦና ባለሙያዎች።

ይህ ሂደት ደግሞ ስነ ልቦናዊ ፍራቻን ሙሉ በሙሉ በማስወገድ ራስን ለስኬት እንደሚያደርስም መስክረዋል።

3. በየዕለቱ መሳካት ያለባቸውን አላማዎች ማስቀመጥ

አንድን እቅድ ለነገ ይደር እያሉ ማጓተት የሰዎችን ደስታ ከሚነጥቁ ነገሮች አንዱ ሲሆን፥ ይህም ሰዎች በሆነ ስሜታዊ አጋጣሚ አዕምሯዊ ችግር ሲፈጠርባቸው የሚከሰት ነው።

አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንደማንኛውም ሰው በየዕለቱ አቅደው ማሳካት የሚገባቸው አላማዎችን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።

በተለይም ወደ ዩኒቨርሲቲ በገቡባቸው የመጀመሪያ ሳምንታት ውስጥ በትምህርት ዓመቱ መነሻ ግብ የተከፋፈሉ የየዕለት እቅዶቻቸውን በማውጣት ለተግባር መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው የሚመከረው።

ከእቅዶቻቸው መካከል አዕምሯዊ ፈተናዎችን የሚቋቋሙባቸውን ስልቶች መንደፍና ከጓደኞቻቸው ጋር መመካከር ያስፈልጋል።

በተለይም ያቀዱትን ግብ የሚያሳኩበትን መንገድ በመንደፍ በትምህርት ዘመናቸው ደስተኛ የሚሆኑበትን እድል መፍጠር ይኖርባቸዋል።

የዛሬ እቅዳቸውን በፍፁም ለነገ ማሳደር የለባቸውም።

4. ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው ራሳቸውን መጠበቅ

አዲስ አካባቢና አዳዲስ ሁኔታዎች በሚስተናገዱበት የዩኒቨርሲቲ ዓለም የሚቀላቀሉ ተማሪዎች አጠቃላይ ጤናቸውን በየዕለቱ ለማስጠበቅ ጥረት ማድረግ አለባቸው።

በተለይም በአዲስነታቸው ምክንያት በሚያጋጥሟቸው አዕምሯዊ ፈተናዎች ሳይደናገጡ ደስተኛና ከጭንቀት ነፃ የሆነ ጊዜ ሊኖራቸው ይገባል።

አመጋገባቸውም ጤንነታቸውን በሚያስጠብቅ መልኩ ነው መሆን ያለበት።

5. በቂ የአዕምሮ እረፍት ማድረግ

ተማሪዎቹ በትምህርትና በተለያዩ ስራዎች ሲደክም የዋለውን አዕምሯቸውን ለማሳረፍ በተመስጦ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ራሳቸውን በፀጥታ ቦታ ማቆየት አልያም ሰላማዊ እንቅልፍን ቢተኙ ይመረጣል።

ይህም በእንቅልፍ ወይም በእረፍት እጥረት ሊከሰት የሚችልን ጭንቀት ይቀንስላቸዋል።

6. ሌሎችን መርዳት

በርካታ የስነ ልቦና እና የስነ አዕምሮ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሌሎችን ሰዎች የሚረዱ ሰዎች ለአዕምሯዊ ችግር የመጋለጥ እድላቸው የጠበበ ነው።

በተለይም አዳዲስ ተማረዎች ለተለያዩ ችግር የተዳረጉ ጓደኞቻቸውን ባላቸው አቅም መርዳታቸው አዕምሯዊ ጤናቸውን ያስጠብቅላቸዋል።

ከዚህም ባለፈ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ጠንካራ እንዲሆን ያግዛቸዋል።

7. ሁኔታዎችን ቀለል አድርጎ ማሰብ

አዳዲስ ነገሮች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉና እነዚህንም ችግሮች በቀላል መንገድ መቅረፍ እንደሚቻል ለአዕምሯቸው ማሳመን የአዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሃላፊነት ነው።

በተለይም ራስን ደካማ አድርጎ አለመሳልና መንፈሰ ጠንካራ መሆን ነገሮችን ቀለል አድርጎ ለማየት ያስችላል።

ይህም ሲባል ፈፅሞ መዘናጋት ደግሞ አያስፈልግም።

8. በተቻለ መጠን አካላዊ እንቅስቃሴን ማድረግ

ተማሪዎች የተነቃቃ ቀንን ለማሳለፍ በማለዳ ተነስተው የሚችሉትን ያህል አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ተመራጭ ነው።

የትምህርት ሰዓት ከመድረሱ በፊት ቀድሞ በመነሳት በእግር ጉዞ ማድረግና ቀድሞ ክፍል ውስጥ መገኘትም ቀናቸውን ብሩህ ያደርግላቸዋል።

ምንጭ፦ www.belfasttelegraph.co.uk