የምግብ መፈጨት ስርዓታችንን የሚያሻሽሉ የምግብ አይነቶች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓመት በዓል ሰሞን ስብነት ወይም ቅባት የበዛባቸውን ምግቦች አዘውትሮ መመገብ በብዛት የተለመደ ነው።

ስብ እና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችን ከተመገብን በኋላም የምግቡ ያለመፈጨት ችግር ሊያጋጥመን የሚችል ሲሆን፥ ከዚህ በተጨማሪም በጉበታችን ላይ እክል ሊፈጥር እንደሚችል ነው የሚነገረው።

የተስተካከለ እና ጤነኛ የምግብ መፈጨት ስርዓት ምግብ በቀላሉ እና በአግባቡ በሰውነታችን ውስጥ እንዲሰራጭ ጤንነታችን የተጠበቀ እንዲሆን ያደርገናል።

ይህንን የምግብ መፈጨት ስርዓታችን ለማፋጠን ይረዱናል የተባሉትን የምግብ አይነቶች ደግሞ ተመራማሪዎች ይፋ አድርገዋል።

እነዚህም፦

እርጎ፦ በእርጎ ውስጥ የሚገኙ ባክቴሪያዎች በአንጀታችን ውስጥ ያሉ ማይክሮ ኦርጋኒዝሞች የተመጣጠኑ እንዲሆኑ በማድረግ የተስተካከለ እና ጤነኛ የምግብ መፈጨት ስርዓት እንዲኖረን ያግዘናል።

ዝንጅብል፦ ዝንጅብል በውስጡ ባለው ንጥረ ነገር ከማካኝነት የአንጀት መቆጣትን ስለሚከላከል የምግብ መፈጨት ስርዓታችን እንዲፋጠን ይረዳናል። 

ለዚህም በየእለቱ ቢያንስ አንድ የሻይ በርጭቆ የዝንጅብል ሻይ መጠጣት ይመከራል።

አጃ፦ አጃ በውስጡ ባለው ንጥረ ነገር የሆድ ድርቀትን ይከላከላል።

በተጨማሪመ በአንጀታችን ውስጥ ያሉ መርዛማ ነገሮችን ጠርጎ በማውጣት አንጀታችን ጤነኛ እንዲሆን እና የምግብ መፈጨት ስርዓታችን እንዲፋጠን ያደርጋል።

አቮካዶ፦ አቮካዶ እንደ ሌሎች የሆድ ድርቀትን ለመከላከል ከሚረዱን የምግብ አይነቶች ተርታ ውስጠ የሚመደብ የፍራፍሬ አይነት ሲሆን፥ ይህም ለምግብ መፈጨት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አፕል፦ አፕል (ፖም) በውስጡ በርከት ያሉ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት በተለያዩ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ያሳያሉ።

አፕል በውስጡ በያዘው ንጥረ ነገርም የሆድ ድርቀትን በከፍተኛ ደረጃ ስለሚከላከል ጤናማ የምግብ መፈጨት ስርዓት እንዲኖረን ያግዘናል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ አፕልን ከ ልጣጩ መመገብ ይመከራል።

ሙዝ፦ ሙዝ በውስጡ በያዘው የፋይበር ንጥረ ነገር አማካኝነት አንጀታችን ንጹህ እንዲሆን ስለሚያደርግ እና ምግብ በአንጀታችን ውስጥ በቀላሉ እንዲዘዋወር ስለሚያደርግ የተስተካከለ እና ጤናማ ይምግብ መፈጨት ስርዓት እንዲኖረን ይረዳናል።

በተጨማሪም የተቅማጥ በሽታ ካጋጠመንም ሙዝን መመገብ ይመከራል።

ስኳር ድንች፦ ስኳር ድንች በፋይበር የበለጸገ የምግ አይነት ሲሆን፥ አንጀታቸን ውስጥ ምግብ በፍጥነት እንዲዘዋወር ያደርጋል ተብሏል።

ስኳር ድንቹን ከነልጣጩ መመገብ ደግሞ የበለጠ ጠቀሜታ እንደሚያሰኝም ተጠቁሟል።

ምንጭ፦ healthdigezt.com