የማንጎ በረከቶች

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2009(ኤፍ ቢ ሲ) ማንጎ ከበሽታ ተከላላይ ምግቦች ውስጥ አንዱ ነው።

የአሜሪካ ተመራማሪዎች የሰሩት አንድ ጥናት ማንጎ የልብ ህመሞችንና የስኳር በሽታን ለመከላከል ያስችላል ብሏል።

ተመራማሪዎቹ ማንጎ ለቆዳ፣ ለአንጎልና ለሆድ የአካል ክፍሎችም ጥቅሙ የላቀ ነው ብለዋል።

በየዕለቱ ማንጎ መመገብ የልብ ህመሞችንና የስኳር በሽታን ለመከላከል ያስችላል።

በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠንንና እና አላስፈላጊ ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠርም ያገለግላል።

የኢሊኖይስ ቴክኖሊጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪዎች ባለፉት 20 ዓመታት በማንጎ እና በዓይነት ሁለት የሰኳር በሽታ ላይ አተኩረው የተሰሩ ሰባት ንጥል ጥናቶችን ተንትነዋል።

በግኝታቸው መሰረትም ማንጎ በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠንን እንደሚቆጣጠር አረጋግጠዋል።

ዓይነት ሁለት የስኳር በሽታ የሚከሰተው ሰውነታችን በቂ የሆነ ኢንሱሊን በማያመነጭበት ጊዜ ሲሆን፥ ዓይነስውርነትን እና አካላዊ ጉዳቶችን ያስከትላል።

በጥናቱ ውስጥ ማንጎ የኮሌስትሮል መጠን እንዲቀንስም ያደርጋል ነው የተባለው።

ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን በዓለም በገዳይነቱ ተጠቃሽ ለሆነ የልብ ህመም እንደሚያጋልጥ ይታወቃል።

በኢንስቲትዩቱ የንጥረ ምግብ ምርምር ማዕቀከል አባል የሆኑት ዶክተር ብሪት ቡርቶን ፍሪማን ማንጎ በዓለም ላይ ተወዳጅ ፍራፍሬ መሆኑን ጠቅሰው፥ በውስጡም በርካታ በሽታ ተከላካይ ንጥረነገሮችን የያዘ ነው ይላሉ።

የሰዎች አካላዊ እንቅስቃሴን የተነቃቃ እንዲሆን የሚያስችሉ የምግብ ይዘቶችንም በውስጡ ይዟል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር ማንጎ የአእምሮ መሳትን ለመከላከል፣ የፀጉርን ጤንነት ለመጠበቅ፣ የአንጀት አካባቢ ህመምን ለመቀነስ ፋይዳው የጎላ መሆኑን በርካታ ጥናቶች ይፋ አድርገዋል።

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ደይሊሜይል