በ10 ሰከንድ ውስጥ ካንሰርን የሚለየው ስክሪብቶ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ10 ሰከንዶች ውስጥ ካንሰርን መለየት የሚችል የኤሌክትሮኒክስ ስክሪብቶ ሰርተናል ብለዋል።

ስክሪብቶው ካንሰርን በ10 ሰከንዶች ውስጥ መለየት ብቻ ሳይሆን፥ የካንሰር እጢውን በቀዶ ህክምና በፍጥነት እና ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ ለማስወገድ እንደሚግዝም አስታውቀዋል።

ስክሪብቶው ምንም አይነት የካንሰር እጢ በሰውነታችን ውስጥ አለመቅረቱንም ያረጋግጣል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ነው ተመራማሪዎቹ የተናገሩት።

“ሳይንስ ትራንስሌሽናል ሜዲስን” ላይ የታተመው ሙከራም፥ በስክሪብቶው የተደረገው ሙከራ 96 በመቶ ፈዋሽነቱ ተረጋግጧል ይላል።

“ማስ ስፔክ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ስክሪብቶው የካንሰር ህዋሶችን ለየት ያለ የህይወት ሂደተን የሚያጠቃ መሆኑም ተገልጿል።

በስክሪብቶው የካንሰር ህዋሱ አለ ተብሎ የሚጠረጠርበት ስፍራ ላይ በሚነካበት ጊዜ ከስክሪብፖው ውስጥ ውሃ መሳይ ፈሳሽ ነገር ይወጣል።

በዚህ ጊዜም ነብስ ያላቸው ህዋሶች ውስጥ የሚገኙ ኬሚካሎች ከስክሪብቶው ወደ ወጣፍ ፈሳሽ ውስጥ የሚሰባሰቡ ሲሆን፥ ስክሪፕቶውም ፈሳሹን መልሱ በመሳብ ምልከታ ያደርግበታል።

ስክሪብቶው ላይ በርካታ ስፔክቶሜትሮች የተገጠሙ ሲሆን፥ ይህም በሰከንዶች ውስጥ በሺህ የሚቆጠሩ ኬሚካሎችን እንዲመረምር ያደርጋል ተብሏል።

በመቀጠልም ስክሪብቶው ለዶክተሮቹ ጤነኛውን አሊያም በካንሰር የተጠቃውን አካል እየመረመሩ ስለመሆኑ በ10 ሰከንዶች ወስጥ መረጃ ያቀብላቸዋል።

በዚህ ጊዜ ለህክምና ባለሙያዎች ፈታኝ የሚሆነው ካንሰሩ እንዳለ ማወቅ ሳይሆን ጤነኛ እና በካንሰር የተጠቃው አካል መካከል ያለውን ድንበር መለየት ብቻ ነው ተብሏል።

ስክሪብቶው ከህክምና በኋላም ምንም አይነት የካንሰር ህዋስ እንዳልቀረ ለዶክተሮቹ ማረጋገጫ እንደሚሰጥም ተነግሯል።

“ማስ ስፔክ” የተባለው ይህ ስክሪብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ የህክምና ባለሙያዎች እጅ እንደሚገባም ተነግሯል።

ምንጭ፦ www.bbc.com