ችላ የሚሏቸው ግን የጤና እክል መፈጠሩን የሚያመላክቱ የሰውነት ላይ ምልክቶች

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የህክምና ባለሙያዎች ሰውነት ላይ የሚታዩ ምልክቶች አንድ ሰው ጤናው ላይ እክል መፈጠር አለመፈጠሩን ማሳያ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ከዚህ አንጻርም ሰውነት ላይ የሚታዩ ምልክቶችን ችላ ባለማለት ጤንነትን መጠበቅ እንደሚገባ ይገልጻሉ።

በርካቶች ልብ የማይሏቸው ግን ደግሞ ከባድ የጤና እክል መፈጠሩን ማሳያ ምልክቶች፤

የቅንድብ ፀጉር መሳሳት፦ ይህ መሆኑን እንደ አጋጣሚ ካዩት ተሳስተዋል።

ይህ ሲሆን የሰውነት እጢዎች በትክክል አለመስራታቸውን ማሳያ መሆኑን የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲዋ ዶክተር ናታሊ አዛር ይናገራሉ።

የሰውነት እጢዎች በአግባቡ አለመስራት ደግሞ በቂ ሆርሞን እንዳያመርቱ በማድረግ ከፍ ያለ ጉዳት ያስከትላል።

ይህም ለከፍተኛ ውፍረት ይዳርጋል ከዚህ ባለፈም በሰውነት መገጣጠሚያዎች አካባቢ የህመም ስሜት መከሰትም የዚህ አንዱ ምልክት ነው።

ከዚህ ባለፈም ለልብና ተያያዥ የጤና እክሎችም ይዳርጋል።

የምላስ በጣም መለስለስና ማበጥ፦ ምናልባት ግጭትና መሰል አደጋ ሳይከሰትብዎት ምላስዎ ካበጠ ሁኔታውን ለሃኪም ማሳወቅ ይኖርብዎታል።

ይህ መሆኑ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት መከሰቱን ማሳያ ነው፤ ቫይታሚን ቢ 12፣ የብረትና ፎሌት ማነስም ስለመከሰቱ ማሳያ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ስለዚህም መደበኛና ከተለመደው ወጣ ያለ ሁኔታ ምላስዎ ላይ ከተከሰተ ለሃኪም ማማከሩን አይዘንጉ።

የእግርና ቁርጭምጭሚት አካባቢ ማበጥ፦ ሁኔታው ምናልባት ጠበብ ያለ ጫማ ከማብዛት አልያም በእንቅስቃሴ ወቅት በሚከሰት ወለምታና መሰል መአጋጣሚ ሊከሰት ይችላል።

ይሁን እንጅ ከዚህ በተለየ መንገድ ከሆነ፥ ስር የሰደደ የልብ ችግር መኖሩን ማሳያ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የእግር አካባቢ ማበጥ ብዙ ጊዜ በሰውነት ውስጥ መወገድ የሚገባው የፈሳሽ ክምችት ሲፈጠር መሆኑንም ነው ባለሙያዎቹ የሚገልጹት።

ይህ ደግሞ የልብና ተያያዥ የጤና እክሎች መከሰታቸውን ማሳያ መሆኑንም ይናገራሉ።

በምሽት ወቅት ቁርጭምጭሚት ሲያብጥ፥ በቀኝ በኩል ያለው የልብ ክፍል ላይ በደረሰው ጉዳት ሳቢያ የውሃና የጨው ክምችት ከሰውነት አለመወገዱን ማሳያም ነውና ችላ አይበሉት።

አይን ላይ የሚታይ ለውጥ፦ በአይን አካባቢ ከቅርጽ ጋርም ይሁን ከአቀማመጥ ጋር ተያይዞ በሂደት የሚፈጠር ለውጥ መኖሩን ማስተዋል ይገባል።

ምናልባት ሲመለከቱ ከተለመደው በላይ በሆነ መልኩ ነጭ ነገር ብቻ የሚያስተውሉ ከሆነም ችግር አለ ማለት ነው።

እንደ ዶክተር አዛር ገለጻ እነዚህ ሁኔታዎች አጋጣሚ ሳይሆኑ የሰውነት እጢዎች ላይ በተፈጠረ እክል ሳቢያ የሚከሰቱ ናቸው።

የሰውነት እጢዎች ከሚገባው በላይ እየሰሩ ከሆነ ይህ አጋጣሚ ይከሰታል።

ይህ ደግሞ ያልተስተካለ የልብ ምት እንዲኖር ያደርጋል፥ ጭንቀት፣ አለመረጋጋት ከልክ በላይ ማሰብና መረበሽም የዚህ ችግር አንድ አካል ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ከፍተኛ ላብና በድንገት የሚከሰት የክብደት መቀነስም የዚህ ምልክት የሚስተዋልባቸው ሰዎች ሊያጋጥማቸው የሚችል ችግር መሆኑንም ዶክተሯ ያነሳሉ።

እናም ይህንና ከላይ የተጠቀሱትን ሌሎች ምልክቶችን ሲያስተናግዱ በቅርብ ወዳለ ሃኪም ጎራ በማለት ማማከር መቻልን ይልመዱ መልዕክታቸው ነው።

 

 

 


ምንጭ፦ ቢዝነስ ኢንሳይደር