ከፍተኛ ጭንቀትና የፍርሃት ስሜት ሲሰማዎት ምን ማድረግ አለብዎት?

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ ጭንቀትና የፍርሃት ስሜት ለማንም ቢሆን የማይመችና ቢቻል መርሳት የሚፈልጉት አይነት ስሜት ነው።

በዚህ ስሜት ውስጥ የሆነ ሰው ጥፍሩን መብላት፣ ከላይ ከላይ መተንፈስና ያልተለመደ የልብ ምት ሊስተዋልበት ይችላል።

ይህ ከውስጥ የመነጨ ከፍተኛ ጭንቀትና ፍርሃት ሲከሰት የሚመጣ መሆኑንም የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ትኩረት ማጣትና ብቻን በመሆን ከሰውም ሆነ ከነገሮች ለመደበቅ መሞከርም በዚህ ስሜት የሚጠቃ ሰው የሚያሳያቸው ምልክቶች ናቸው።

ባለሙያዎቹ በየቀኑ የሚያጋጥም መሰል ስሜትን ለማስወገድ የሚረዱ መንገዶችንም ይጠቁማሉ፤

ለዚህ ስሜት ሊዳርግ የሚችልን አጋጣሚ መለየት፦ በከፍተኛ ጭንቀትና የፍርሃት ስሜት ውስጥ የሆነ ሰው የሆነ አደጋ አይቀሬ እንደሆነና እንደሚከሰትበት ያስባል።

ይሁን እንጅ ይህ በሃሳብ ደረጃ የሚያስጨንቀው የፍርሃትና ጭንቀት ስሜት በእውነታው የማይከሰት ሲሆን ይስተዋላል።

ከዚህ አንጻርም የሚያስፈሩና የሚያስጨንቁ ስሜቶችን ከማስተናገድ ባለፈ ምን ያክል በእውነቱ አለም እንደሚከሰቱና ምን ያክሉ ሃሳብ ወለድ ብቻ እንደሆኑ መለየት መቻል።

ይህ ሲሆን ሁኔታዎች አጋጣሚ አልያም እውነታ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ ይረዳል።

ሰውነትን ማዝናናትና በጥልቅ አየር መሳብ፦ ቀለል ያሉና ጡንቻንና ሰውነትን የሚያፍታቱ ማዝናኛዎችን ማድረግ መቻል፥ ያለምንም ጭንቀት የተሻለ እንዲያስተውሉና እንዲያስቡ ያስችልዎታል።

ከዚህ ባለፈም ብቻዎን በመሆን በጥልቅ በመተንፈስ ሰውነትዎን ለማዝናናት መሞከር።

ይህን ስሜቱ ከመከሰቱ በፊትም ሆነ በሚከሰትበት ወቅት ማድረጉ የተሻለ አዋጭ መንገድ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይመክራሉ።

በጥልቅ መተንፈስ፣ አየር መሳብና ሰውነትን በማፍታታት ማዝናናት መቻል፥ በፍርሃትና ጭንቀት ወቅት የተሰበሰቡ የሰውነት ጡንቻዎችንና ክፍሎችን ዘና ለማድረግ ያግዛል።

ይህም ከዚያ ስሜት በቶሎ እንዲወጡ ለማገዝ ይረዳልና ይጠቀሙበት፤ ዘወትር በዚህ አይነት ስሜት ሲገቡ መሰል አጋጣሚዎችን መጠቀም ይልመዱ።

ትኩረት መሰብሰብ፦ በዚህ ወቅት ትኩረትን ሰብሰብ አድርጎ ነገሮችን ለመገንዘብ መሞከር የመጀመሪያ አማራጭ ማድረግ።

እየሆኑ ያሉ ነገሮችን በአግባቡ ለመረዳት መሞከር፤ ምናልባት የፍርሃት ስሜት ነግሶ ከሆነ ከጭንቀት በፀዳ መልኩ መሆን አለመሆኑን መለየት።

ከዚህ አንጻርም ሁኔታውን ለመረዳትና ለመለየት መሞከር ከተከሰተብዎት አላስፈላጊ ስሜት ይወጡ ዘንድ ይረዳዎታል።

ስሜቱን መቀበልና ህይዎትዎ ላይ ብቻ ማተኮር፦ ምንጊዜም ቢሆን መጥፎ አጋጣሚዎች አሉታዊ ሃሳቦች በህይዎት ውስጥ አይቀሬ መሆናቸውን አምኖ መቀበል።

በህይዎት እያሉ የሚደሰቱትን ያክል የሚከፉባቸውና አሉታዊ ነገሮችን የሚያስቡባቸው አጋጣሚዎች ስለመኖራቸው ተዘጋጅቶ መጠበቅ።

በዚህ የፍርሃትና ጭንቀት ስሜት ውስጥ ያሉ ሰዎችንም፥ በግድ ስሜቱን ርሱት ከማለት ይልቅ ስሜቱ የተለመደ እንደሆነ ማስረዳትና እንዲያስተናግዱት መምከር።

ከዚያ ባለፈ ግን ህይዎታቸው ላይ ቀዳሚ ሊሆኑ የሚገቡና ሊያተኩሩባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ በማስረዳት ሁኔታውን ቀለል አድርገው እንዲያዩት መንገር እንጅ አለመጫን።

ሁኔታውን መላመድ፦ ይህ ደግሞ ከመቀበልም አልፎ ያጋጠመዎትን ሁኔታ መጋፈጥን ይጠይቃል።

ለዚህ ስሜት የሚዳርግዎትና የሚያስፈራዎት ነገር ምንም ይሁን ምን መጋፈጥ መቻል፥ ይህን ማድረግዎ አብረው እየኖሩም ከስሜቱ ለመውጣት በእጅጉ ይረዳዎታል።

የፍርሃት ስሜት ሁልጊዜም ቢሆን ከሚፈሩትና ከሚጠሉት ሰው፣ ሁኔታ እና አካባቢ እንዲሸሹና እንዲርቁ ሊያስገደድዎት ይችላል።

ዘወትር የሚፈሩትና የሚሸሹት ነገር በእውነተኛው አለም የሚያስቡትን ያክል አስፈሪና አደገኛም ላይሆን ግን ይችላል።

ከዚያ ይልቅ ግን ሁኔታውን መጋፈጥና መታገልን መልመድ፥ በሽሽት ራስን ማግለል ከመጠቃት ውጭ የሚያተርፉት ነገር የለምና ምንም ነገር ቢመጣ ወደ ኋላ ከማለት ይቆጠቡ።

የራቁት ሰው፣ ሃሳብም ሆነ ሁኔታ ጊዜ ይፍጅ እንጅ መልሰው ማግኘትዎ አይቀርም፤ ስለዚህ በተቻለ መጠን አንድን ነገር ፈርቶ ከመራቅ ሁኔታውን መላመድ፤ ግን ደግሞ ተጋፍጦ ማሸነፍን ምርጫዎ ያድርጉ።

ከላይ ከተቀሱት በተጨማሪም መሰል ስሜቶችን ሲያስተናግዱ ሁኔታዎችን መቆጣጠርና ማስወገድ የሚችሉበት አቅም እንዳለዎት በማሰብ ወደ መፍትሄ መግባቱም ይመከራል።

ምን ጊዜም ቢሆን ስጋትና አደጋን መቀነስ አላማዎ አድርገው በመነሳት ለችግሩ መፍትሄ ማበጀት እንጅ በነገሩ መብሰልሰልን ያቁሙ።

አስፈላጊ ሆኖ እስተገኘ ድረስም ወዳጅ የሚሉትን ሰው በማዋየት ከችግሩ መውጫ መንገድን ማግኘት ይችላሉ።

በተጨማሪም ብቻን አለመሆንና ቀለል ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግም ከዚህ ስሜት ለመውጣት ያግዛሉና ይጠቀሙባቸው።

 

 

 

ምንጭ፦ psychologytoday.com/