መጥፎ ስሜቶችን አምኖ አለመቀበል የስነልቦና ጤና ላይ የበለጠ ጉዳት ያስከትላል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስሜታችን ጥሩ ባልሆነብ ጊዜ ተስፋ ያዘሉ መልካም ነገሮችን ማሰብ ለወደፊት ህይወት ጥሩ መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች መጥፎ ስሜቶቻቸውን የሚቆጣጠሩና በአዎናንታዊነት የሚቀበሉ ሰዎች የተሻለ ስነልቦናዊ ጤና እንደሚኖራቸው አረጋግጠናል ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የስነልቦና ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰርና የጥናቱ ከፍተኛ አዘጋጅ ኢሪስ ማውስ፥ መጥፎ ስሜቶችን በአዕምሮ ውስጥ ቦታ ከመስጠት ይልቅ ለማጥፋት መሞከርና በመልካም ጎናቸው መቀበል የተሻለ መሆኑን ጥናታችን ጠቁሟል ነው ያሉት፡፡

አሉታዊ ስሜት የሚፈጥሩ ነገሮችን እንደ መጥፎ አጋጣሚ በመቁጠር በተደጋጋሚ ማሰብ ራስን ለከፋ ጉዳት ማጋለጥ ነውም ይላሉ፡፡

ኢሪስ ማውስ የሰሜት ተቀባይነትን እና የስነልቦና ጤና ተዛምዶን በዳሰሱበት ጥናት 1 ሺህ 300 ወጣቶችን አሳትፈዋል፡፡

በጥናቱ ማጠቃለያ አሉታዊ ስሜታቸውን ከመቀበል ይልቅ በመጥፎ አጋጣሚነት የሚፈርጁ ሰዎች ለስነልቦናዊ ቀውስ ተዳርገዋል ተብሏል፡፡

በስድስት ወር ውስጥ በተሰራው ጥናት በመጥፎ ስሜቶች የሚበሳጩና፣ ቅር የሚላቸው ሰዎች ለከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት የመዳረግ እድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡

በመሆኑም ሰዎች የተሻለ ስነልቦናዊ ጤንነትን እና የህይወት ስኬታማነትን ለማምጣት መጥፎ ስሜቶቻቸውን አምኖ መቀበልና ከአዕምሮ ለማስወገድ መጣር ይገባቸዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡- www.sciencedaily.com