ሳምባዎ መጎዳቱን የሚያሳዩ ምልክቶች

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 4 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) እንደ ሲጋራ ማጨስ እና መሰል ደባል ሱሶች የሳምባ ደህንነትን የሚጎዱ ልማዶች ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ከአካባቢ ጽዳት ጋር ተያይዞ በሚመጣ ባክቴሪያና ኢንፌክሽን ሳቢያም ይህ የጤና እክል እንደሚከሰት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የአየር ብክለት እና መሰል አጋጣሚዎችም ለዚህ ችግር ይዳርጋሉ፤ ይህን የጤና ችግር ለመከላከል ምልክቶቹን አስቀድሞ መለየትና ማወቅ ያስፈልጋል።

ይህን ማድረጉ ደግሞ ከከፋው የሳምባ ካንሰር ራስን ለመከላከልና ለመጠበቅ ይረዳል ይላሉ ባለሙያዎቹ።

ከዚህ በታች የተጠቀሱት ምልክቶች ደግሞ ሳምባ መጎዳቱን ማሳያ ምልክቶች ናቸውና ያስተውሏቸው።

ተከታታይ ሳል፦ በጣም ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ሳል ካለብዎት ሳምባዎ ላይ እክል መከሰቱን ማሳያ ነው፤ ምናልባት ይህን ሳልዎን በህክምናም ሆነ በሌላ መንገድ ለማስታገስ ሞክረው ለውጥ የማያሳይ ከሆነ ደግሞ ሃኪም ማማከር ይኖርብዎታል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሲስሉ እስከ ትክሻዎ በሚደርስ ሁኔታ ደረትዎ አካባቢ ህመም የሚሰማዎ ከሆነም ችግሩ መከሰቱን ምልክት ነው።

ሲያስልዎት በአክታ መልክ የሰውነት ፈሳሽዎን ሊያጡ የሚችሉበትን አጋጣሚ ለመቀነስ ደግሞ እንደ ውሃ ያሉ ፈሳሽ ነገሮችን በብዛት ይውሰዱ።

ያልተስተካከለ አተነፋፈስ፦ በስራም ይሁን በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆነው በተጨናነቀ መልኩ ቁርጥ ቁርጥ ያለ አተነፋፈሰም የዚህ ችግር አንዱ ማሳያ መሆኑ ይነገራል።

ይህ የትንፋሽ መቆራረጥና ያልተስተካከለ አተነፋፈስ ሳምባ ከተለመደው በላይ በሆነ መልኩ አየር ለማስወጣትና ለማስገባት ከልክ በላይ ራሱን ሲያስጨንቅ የሚከሰት አጋጣሚ ነው።

እንዲህ አይነት አጋጣሚ ሲከሰት ታዲያ ወደ ህክምና ተቋም ማምራትና ሃኪም ማማከር ከዚያ ባለፈ ግን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራትና ካለብዎት ከደባል ሱስ መራቅ።

የአክታና ንፍጥ መብዛት፦ ይህ መሆኑ ደግሞ መልካም አይደለም ምክንያቱም ከአፍንጫ የሚወጣ ንፍጥ እና ሲያስሉ የሚኖር አክታ ለሳምባ ጠንቅ የሆኑ ባክቴሪያዎች መደበቂያ ስፍራ እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል።

ጉንፋን ሲይዝዎት ይህ አይነቱ አጋጣሚ የተለመደ ቢሆንም ከዚህ በተለየ መንገድ ሲሆን ግን የጤና አይደለምና መታየቱ አይከፋም።

ከዚህ ባለፈም የንፍጥንም ሆነ የአክታን ቀለም፣ የውፍረት መጠን፣ ብዛትና ምናልባት የተለየ ጠረን ይኖረው እንደሆነ ያንን ማስተዋልም ተገቢ ነው።

ምናልባት ከወትሮው በተለየ ወደ ቢጫነት አልያም አረንጓዴ አይነትና ደም የቀላቀለ ከሆነም፥ አጋጣሚ ሳይሆን ሳምባዎ ላይ የደረሰ የጤና እክል አለና መታየቱ የግድ ይሆናል።

ወፈር ያለ ደም የቀላቀለ ንፍጥ መናፈጥ ሳምባ በካንሰር መያዙን አልያም ስር የሰደደ ብሮንካይት እና የመተንፈሻ አካል ችግር መከሰቱን ማሳያ ነውና ቸልታ አያስፈልገውም።

ከዚህ ባለፈም ሲተነፍሱ የማፏጨት አይነት ድምጽ ያለው ትንፋሽ ማውጣትና ከደረትዎ ጀምሮ በቀጭን የሚወጋ አይነት ስሜትም ይህ ችግር መከሰቱን ማሳያ ነው።

ይህ ሁኔታ ብዙ ጊዜ የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎች መጥበብ ሲከሰት የሚፈጠር አጋጣሚ ነው፤ ይህ ሁኔታ በአንድ አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል።

በተደጋጋሚ እና ለቀናት የቆየ ከሆነ ግን ምናልባትም፥ የአስም፣ ከባድ የመተንፈሻ አካል ጉዳት ብሎም የሳምባ ካንሰር ምልክት ሊሆን ይችላል።

እግር አካባቢ የሚከሰት እብጠት፦ በታችኛው የሰውነት ክፍል በተለይም እግር ላይ የሚከሰት እብጠት ከሳምባ ጋር ተያያዥነት ያለው የጤና እክል መከሰቱን ማሳያ ይሆናል።

በሳምባ ስራ መስተጓጎል ምክንያት ልብም በአግባቡ ደም መርጨት አይችልም፥ ይህ ደግሞ ጉበትና ኩላሊት በአግባቡ ስራቸውን እንዳይሰሩ ያደርጋቸዋል።

ይህ ሲሆን ደግሞ ፈሳሽ በሰውነት ያለአግባብ እንዲከማችና እንዲንቀሳቀስ ይሆናል።

አላስፈላጊ ፈሳሽ ከሰውነት እንዳይወጣ በማድረግም ሰውነት በቀላሉ እንዲመረዝ አጋጣሚን ይፈጥራል፤ በዚህ ሳቢያም ጉልበትና የታችኛው የሰውነት ክፍል ላይ እብጠት ይፈጠራል።

ማለዳ ላይ የሚሰማ ራስ ምታት፦ ማለዳ ሲነቁ ብዥታ የታከለበት ራስ ምታት ካጋጠምዎት ውስጣዊ ችግር እንዳለ ማሰቡ አይከፋም።

ከሳምባ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ካለብዎት ማለዳ ሲነቁ ዘወትር ብዥታ የታከለበት ራስ ምታትና በደንብ አለማስተዋል ሊከሰት ይችላል።

ይህ ደግሞ ሌሊቱን በአግባቡና በደንብ ካለመተንፈስ ጋር ተያይዞ የመጣ ችግር ነው፤ ይህ ችግር ደግሞ የበዛ ካርበን ዳይ ኦክሳይድ በሰውነት እንዲከማች ያደርጋል።

ይህ የካርበን ዳይ ኦክሳይድ ክምችት ደግሞ በጭንቅላት ውስጥ የሚገኙ የደም ቧምቧዎች ከልክ በላይ እንዲሰፉ በማድረግ ከባድ ራስ ምታት፣ ብዥታና መጨነቅ ወይም የመወጣጠር ስሜት እንዲሰማ ያደርጋል።

ከፍተኛ ድካም፦ በቂ እረፍት አግኝተው እያለ አሁንም አሁንም ድካም የሚሰማዎት ከሆነም ሰውነትዎ ለመጎዳቱና የጤና እክል እንዳለብዎት ማሳያ ነው።

ይህን መሰል ችግሮች ደግሞ በአብዛኛው ከሳምባ ጋር የተያያዙ ይሆናል።

ሳምባ በትክክል ካልሰራ የድካም ስሜት የተለመደ ነው፥ ሳምባ በቂ ኦክስጅን ሳያገኝ ቀረ ማለት ሌሎች የሰውነት ክፍሎች እንዲዳከሙ ያደርጋልና።

ይህ ሲሆን ደግሞ ከልክ በላይ ይደክማሉ ይህ ደግሞ በሂደት ከፍ ያለ ጉዳት ያስከትላል።

ከእንቅልፍ ጋር የተያያዙ ችግሮች፦ ምናልባት አልጋ ላይ ዘና ብለው መተኛት ፈልገው እንቅልፍ እምቢ እያለ ካስቸገረዎት እና ሁኔታው ከተደጋገመ የጤና እክል ተፈጥሯል ማለት ነው።

በዚህ ሁኔታ እንቅልፍ ሲያጡ ሌላ ቦታ ላይ መሞከርና እንደ ወንበር ባሉ መገልገያዎች ላይ መተኛትም በአብዛኛዎቹ ዘንድ ይስተዋላል።

ይሁን እንጅ ይህ አጋጣሚ የጤና አለመሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ ምክንያቱም አልጋ ላይ ቀጥ ብሎ መተኛት ሳምባ በደምብ እንዲሰራ ያስገድደዋል።

በትንሽ ቦታ ላይ መተኛቱ ግን ያን ያክል አያስጨንቀውም፥ ከሳምባ ጋር የተያያዘ የጤና እክል ካለብዎትም አልጋ ላይ ሲተኙ ሳምባ በደምብ መስራት ስላለበት እንቅልፍ በአግባቡ አይተኙም።

ምክንያቱም ሳምባ ተጎድቷልና እንቅልፍ ይተኙ ዘንድ የሚያስፈልገውን ስራ የሚሰራበት አቅም የለውም፤ እናም መሰል አጋጣሚዎች ችላ ሳይሉ ሃኪም ያማክሩ።

ሲጋራ አለማጨስ፣ በተበከለ አካባቢ አለመኖር፣ በቤት ውስጥ አትክልት መትከል (ንጹህ አየር ለማግኘት ይረዳል)፣ ከፍ ያለ የኬሚካል ይዘት ያላቸውን ምርቶች ለጽዳትም ሆነ ሌሎች ነገር በብዛት አለመጠቀም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ጤናማ አመጋገብ እና የአኗኗር ዘይቤ የሳምባ ጤንነትን ለመጠበቅ ይረዳል።


ምንጭ፦ top10homeremedies.com