በበለፀጉ ሀገራት በብቸኝነት ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን የበለፀጉ ሀገራት ብቸኝነትን የሚያቀነቅን ባህል የሚበረታታባቸው እንዲሁም እናትና አባት በየዕለቱ የሚፋቱባቸው በመሆኑ ወጣት ልጆች ብቸኝነትን እንዲያዘወትሩ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡

ከሰሞኑ ይፋ የሆኑ ሁለት ጥምር ጥናቶች ብቻቸውን መኖር የሚፈልጉ ሰዎች በማህበራዊ ግንኙነት የተሻሉ ከሆኑት 50 በመቶ ቀድመው የመሞት እድል እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

ጥናቶቹ በአሜሪካ አንድ ሶስተኛው ማህበረሰብ ብቸኝነት የሚያጠቃው ሲሆን በብሪታኒያ 18 በመቶ ወጣቶች ብቸኝነት እንደሚሰማቸው አመላክተዋል፡፡

ራስን ከማህበረሰቡ አግልሎ መኖር ከጤና ጋር ያለው አሉታዊ እና አዎንታዊ ግንኙነት በጥናቶቹ ተብራርቷል።

በተለይም ብቸኝነት የሰው ልጅ በህይወት ከሚቆይበት አማካይ እድሜ በጣም ቀድመው እንዲሞቱ ምክንያት መሆን እና አለመሆኑ ላይ አተኩራል፡፡

በብሪግሃም ያንግ ዩኒቨርሲቲ የስነልቦና ፕሮፌሰሯ ጁሊያን ሆልት ሉስታንድ፥ በአሜሪካ የስነልቦና ባለሙያዎች ማህበር ኮንፈረንስ ላይ ከዚህ ቀደም በተሰሩ 148 ጥናቶች ላይ የተመሰረተ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በእነዚህ ጥናቶች ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት ያላቸው ብቸኝነትን ከሚዘወትሩት 50 በመቶ በህይወት የመቆየት እድላቸው ከፍ ያለ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሁለተኛው የጥምር ጥናት ግኝት ውስጥ በ70 ምርምሮች ላይ ተመስርቶ የቀረበ ሲሆን፥ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስያ እና አውስትራሊያ የሚኖሩ ከ3 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ሰዎችን አሳትፏል፡፡

በግኝቱ ራስን ከማህበረሰቡ መነጠል እና በዘላቂነት በብቸኝነት መኖር በወጣትነት እድሜ ለመሞት እንደሚዳርግ ተጠቅሷል፡፡

በዓለም ላይ በአብዛኞቹ ሀገራት የሚኖሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቸኝነት ከማህበራዊ ተሳትፏቸው የሚነጥል ክፉ በሽታ እየሆነ መምጣቱን መናገራቸው ተብራርቷል፡፡

ባደጉት ሀገራት ራስን የማግለል ባህል እየተዘወተረ መሆኑ የሰዎችን በህይወት የመቆየት እድሜ የሚቀንስ አሳሳቢ አደጋ ለመደቀኑ ማሳያ ነው ተብሏል፡፡

በተለይም ጥቂት ልጆች ያላቸውና ትዳራቸውን የፈቱ ሰዎች ብቸኝነትን በመምረጥ ቀዳሚዎቹ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

ባሳለፍነው ጥር ወር የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት በብቸኝነት ምክንያት ሊበራከት የሚችል ራስን የማጥፋት ድርጊትን ለመከላከል አዲስ መመሪያ እንዲዘጋጅ መወሰናቸው ይታወቃል፡፡

በመመሪያው መሰረትም አዲስ ኮሚሽን ተቋቁሞ ብቸኝነት በሚያጠቃቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን እያስተባበረ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ከማህረበረሰቡ ራስን ነጥሎ በብቸኝነት የመሰቃየት እና ህይወትን አደጋ ላይ መጣልን ተከትሎ የሚጨምረውን ሞት ለመቀነስ ሰዎች ማህበራዊ ህይወትን እንዲላመዱ ማድረግ፣ በገንዘብ መደገፍ እና የተለያዩ ማህበራዊ ትስስሮችን መፍጠር ይገባል ይላሉ የስነ ልቦና እና ማህበረሰብ ሳይንስ ምሁራን።

ምንጭ፦ https://qz.com/