ዘመናዊ ስልኮች የታዳጊዎችን የደስተኝነት ስሜት እያራቀ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን አሁን ታዳጊ እና ወጣቶች ጊዜ ካመጣው ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር ያላቸው ቁርኝት የጠበቀ ሆኗል።

ይህ ሁኔታ ደግሞ ታዳጊዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በአሜሪካ ሳንዲያጎ ዩኒቨርሲቱ የተደረገ ጥናትም ታዳጊዎች እና ወጣቶች በዚህ ሳቢያ ደስታ የራቃቸው መሆናቸውን ያሳያል።

በዩኒቨርሲቲው የስነ ልቦና ተማራማሪዋና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጃን ትዌንጅ ከፈረንጆቹ 19 95 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ በተወለዱ ታዳጊ እና ወጣቶች ላይ ይህ ሁኔታ እንደሚስተዋል ያነሳሉ።

እርሳቸው ከባልደረቦቻቸው ጋር ባደረጉት ጥናት የበዛው የዘመናዊ ስልክ ቁርኝት ታዳጊና ወጣቶችን ለብቸኝነት በመዳረግ ደስተኝነታቸውን እንዲያጡ ማድረጉን ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰሯ አሁን ላይ አብዛኛዎቹ ታዳጊና ወጣቶች ዘመናዊ ስልኮችን በመጠቀም በማህበራዊ ትስስር ገጾች በራሳቸው ጉዳይ ስለሚጠመዱ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የላላ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ይህ ደግሞ የእርስ በርስና የአብሮነት ቆይታ ጊዜውን በማሳነስ ለበዛ ብቸኝነትና በሂደትም ደስተኝነታቸውን በማሳጣት ለጉዳት ይዳርጋቸዋልም ነው የሚሉት።

ምናልባት የዚህኛው ትውልድ ደህንነት ከአካላዊ አቋም ጋር የተያያዘ ብቻ መሆኑንም ነው የሚያነሱት፤ ከዚያ ውጭ እጅግ የላላ ማህበራዊ መስተጋብር ባለቤት መሆናቸውን በመጥቀስ።

አብሮ መዋሉ ሳይሆን እንደ ጓደኛም ሆነ እንደ ወዳጅ ልብ ለልብ የመገናኘታቸው አጋጣሚ አናሳ ነውም ይላሉ፤ ለዚህ ደግሞ ዘመናዊ ስልኮችና ማህበራዊ ሚዲያዎች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ይጠቅሳሉ።

አሁን ላይ ያሉ ታዳጊ እና ወጣቶች ከጓደኞቻቸው ጋር በአካልና ፊት ለፊት ተገናኝተው አብረው ከማሳለፍ ይልቅ ስልክና ማህበራዊ ሚዲያዎችን ይጠቀማሉ።

ይህ ደግሞ ከፍ ያለ የስነ ልቦና ጫና ይፈጥራል ባይ ናቸው፤ ከዚህ በፊት የተደረጉ ጥናቶችም ይህን እንደሚያሳዩ ይጠቅሳሉ።

የስነ ልቦና ጫና ደግሞ ታዳጊዎቹን በጊዜ ሂደት ከአዕምሮ ጋር ለተያያዙ የጤና እክሎች ይዳርጋቸዋል።

ይህ አጋጣሚ ወደ ብስጭትና ድብርት በማምራት ራስን ወደማጥፋት ስሜት እንዲገፋፉ የማድረግ አጋጣሚው ከፍ ያለ እንደሚሆንም ያስረዳሉ።

ቤተሰብ ልጆቻቸው ከቤት ወጣ ብለው ሲዝናኑ አልያም መኪና እያሽከረከሩ መሄዳቸውን በማሰብ ብቻ ይጨነቃሉ።

በተቃራኒው ቤት ውስጥ ብቻቸውን ከስልካቸው ጋር የሚያሳልፉት ምንም እንደማይሆኑ ያስባሉ፤ ይህ ግን ስህተት ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ትዌንጅ።

ምክንያቱም ብቻቸውን ማሳለፋቸው መንገድ ላይ ወጥተው ከሚከሰት አደጋ እንጅ ከአዕምሮ መቃወስ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች አይታደጋቸውምና።

እናም ወላጆች ልጆቻቸውን ለመዝናናት ልከው ከሚጨነቁት በተሻለ ብቻቸውን የሚያሳልፉ ልጆቻቸውን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እንዲከታተሉት ይመክራሉ።

ለታዳጊዎች ደግሞ ከስልካቸው ጋር ያለው ቁርኝት ጉዳት እንዳያስከትልባቸው በየመሃሉ እንቅስቃሴ ማድረግና በአብዛኛው በብቸኝነት እንዳያሳልፉ ይመክራሉ።


ምንጭ፦ www.npr.org