ሩጫና ክብደት የማንሳት ስፖርትን በተመሳሳይ ቀን መስራት እንደሌለብን ተመራማሪዎች ያስጠነቅቃሉ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሩጫ እና ክብደት የማንሳት ስፖርትን በተመሳሳይ ቀን አንድ ላይ ጠምራችሁ መስራት የለባችሁም ይሉናል ተመራማሪዎች።

የስፖርቱ ዘርፍ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት፥ በአሁኑ ጊዜ የአካል ብቃት እና የሰውነት ማጠንከሪያ ስፖርቶችን አንድ ላይ ጠምሮ መስራት ውጤቱ መልካም እንደሆነ በርካታ ሰዎች ያምናሉ።

ነገር ግን ይህ ሊሆን የሚችለው በሁለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች መካከል ሰውነታችን ከድካም ሙሉ በሙሉ እንዲያገግም ቢያንስ የ24 ሰዓት እረፍት ከሰጠነው ብቻ ነው ሲሉም ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

በአውስትራሊያ ኩዊንስላንድ ጀምስ ኮክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ከክብደት ማንሳት ጋር ተያይዞ የሚከሰተው የሰውነት መዛል ለበርካታ ቀናት እንደሚቆይ ነው የሚናገሩት።

ይህ ደግሞ እንደ ሩጫ ያሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ያለ በቂ እረፍት በምንሰራበት ጊዜ ጥንካሬያችንን ሊጎዳ ይችላል ብለዋል።

የስፖርት ዘርፍ ተመራማሪው ዶክተር ኬንጂ ዶማ፥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በምንሰራበት ጊዜ ዋናው የሚያግባባን ነገር ስፖርቱ ለሰውነታችን ጥንካሬን እየገነባ ነው የሚለው መሆን አለበት ይላሉ።

ሆኖም ግን ሩጫ እና ክብደት የማንሳት ስፖርት በሚሰራበት ጊዜ በሁለቱ መካከል በቂ እረፍት ከሌለ የሰውነታችንን ጥንካሬ ከመጎልበት ይልቅ ጥንካሬውን እየተጎዳ ይሄዳል ይላሉ ዶክተር ኮንጂ ዶማ።

በተጨማሪም እንደ ክብደት ማንሳት ያሉ የሰውነት ማጠንከሪያ ስፖርትን በምንሰራበት ጊዜ የሚፈጠር የስነ ልቦና ጫና ስላለ ይህንን በመቀነስ ሌላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለመስራትም ቢያንስ የ24 ሰዓት እረፍት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

እነዚህን የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች አንድ ላይ መስራት ጠቀሜታ ቢኖረውም ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ብናደርግ መልካም ነው ሲሉም ይመክራሉ።

የሰውነት ማጠንከሪያ ስፖርቶች ውስጥ ክብደት ማንሳት፣ ፑል አፕ፣ ፑሽ አፕ እና ሌሎች የስፖርት አይነቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፥ ሰውነታችን ወስጥ ያለን የስብ መጠን ለመቀነስ፣ ካሎሪ ለማቃጠል እና ጡንቻ ለማጠንከር በብዛት ይሰራል።

ከዚህ በተጨማሪም አጥንታችንን ለማጠንከር የሚረዳን ሲሆን፥ ከአጥንት ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የጤና እክሎች የመጋለጥ እድላችንንም ይቀንሳል።

ኤሮቢክስ ተብለው የሚጠሩት የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ደግሞ የእግር ጉዞ፣ ሩጫ፣ ሳይክል መንዳት፣ የውሃ ዋና እና መሰል እንቅስቃሴዎችን ያካትታል።

ይህ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴ አላስፈላጊ ካሎሪን ለማቃጠል፣ የደም ግፊትን ለመቆጣጠር እና የልብ ጤንነትን ለመጠበቅ ይረዳናል።

ጤናማ የሆኑ አዋቂ ሰዎች በሳምንት ውስጥ በአማካኝ ለ150 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እንዲሰሩ ይመከራል።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk