ስንቀመጥ እግራችን የሚይዘው ቅርፅ ስለ ባህሪያችን የሚለው ይኖር ይሆን?

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰውነት እንቅስቃሴ የሰዎችን ማንነት እና ባህሪ ለመገመት ፍንጭ እንደሚሰጡ ነው የስነ ልቦና ባለሙያዎች የሚናገሩት።

እጁን እያወራጨ የሚያወራ ሰው የተረጋጋ እና ፀባየ መልካም እንዳልሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል።

በምንቀመጥበት ወቅት እግራችን የሚይዘው ቅርፅም ስለ ባህሪያችን የሚገልፀው በርካታ ነገር እንዳለ ጥናቶች አሳይተዋል።

አቀማመጥ “A” - የኋላ እግርን አስፍቶ መቀመጥ

ይህን አይነት አቀማመጥ የሚያዘወትሩ ሰዎች እንከኖቻቸውን ችላ ብሎ ማለፍ ከዚያ ችግር የመውጫ ዋነኛ ዘዴ መሆኑን ያምናሉ።

ከዚህም ባሻገር ችግሮቻቸውን ወደ ሌሎች ሰዎች የሚያጋቡ እና ጊዜያቸውን የማይሰጡ መሆናቸውም ይነገራል።

ጉልበትና ጉልበታቸውን አጋጥመው እግራቸውን ከወደ ኋላ ሰፋ አድርገው የሚቀመጡ ሰዎች ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ እንደ ህፃን ቢያደርጋቸውም የፈጠራ ችሎታቸው እና ተጫዋችነታቸው ማራኪ ነው ተብሏል።

ከመናገራቸው በፊት አያስቡም፤ የተናገሩት ነገር የሚያስቀይም መሆኑን የሚረዱት ከረፈደ ነው።

ቅርፅ “B” - እግርን ማጣመር

እግራቸውን አጣምረው የሚቀመጡ ሰዎች ደግሞ በአዳዲስ እና መልካም ሀሳቦች የተሞሉና በስራ ገበታቸው ሁልጊዜ አድናቆት የሚቸራቸው ናቸው ተብሏል።

ብዙ ጊዜ ተመሳሳይ ስራ እና አውድ አይመቻቸውም፤ ጉዞ ማድረግ እና አዳዲስ ጓደኞችን መፍጠር ይወዳሉም ነው የተባለው።

ደስታ ባልፈጠረላቸው የፍቅር ግንኙነት እና ጉልበታቸውን በሚጨርስ ስራ ላይ ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እንደማይሹም ነው የሚነገረው።

ቅርፅ “C” - እግርን አጋጥሞ ከወደ ጉልበት ማስፋት

በዚህ መልኩ የሚቀመጡ ሰዎች አዲስ ነገር ሲገዙ ለቀናት ስለገዙት ነገር ያስባሉ፤ ሁሉም ነገር ምሉዕ እና ውጤታማ እንዲሆንም ይፈልጋሉ።

በልብስ፣ ጫማ፣ ሽቶ እና የቤት እቃ ምርጫም ለመወሰን የሚቸገሩ መሆናቸው ይነገራል።

አስቸጋሪ ሁኔታን በመላመድ ረገድ ብዙ አይቸገሩም የተባሉት እነዚህ ሰዎች፥ በስራ ገበታቸው እና ሰዎች ሲያናግሯቸው ትኩረት በመስጠት በኩል ክፍተት እንዳለባቸው ተጠቁሟል።

ቅርፅ “D” – ሁለት እግርን በእኩል ደረጃ ከፈት ማድረግ

እግራቸውን በእኩል ደረጃ ከፈት በማድረግ የሚቀመጡ ሰዎች ማርፈድ እና የሚያረፍዱ ሰዎችን ይጠላሉ፤ የተረጋጉ እና ጎበዝ መሆናቸውም ይነገራል።

ከሰዎች ጋር መነታረክ የማይወዱ ሲሆን፥ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ስሜታቸውን መግለፅም አይወዱም።

በዚህ አኳኋን የሚቀመጡ ሰዎች ግልፅ እና የሚሰማቸውን የመግለፅ ችግር የሌለባቸው ናቸው።

የማህበራዊ ግንኙነታቸው ግን የላላ ሲሆን ተጠራጣሪነታቸው ብቸኝነትን እንዲመርጡና ከቤታቸው መውጣት እንዲጠሉ አድርጓቸዋል።

ትችት በግላዊ አመለካከታቸው ላይ የተቃጣ ጥቃት ስለሚመስላቸውም የሌሎች ሰዎችን አስተያየት አይቀበሉም ተብሏል።

ቅርፅ “E” – ሁለቱንም እግራችን ወደ አንድ አቅጣጫ ማዘንበል

እግራቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ አዘንብለው የሚቀመጡ ሰዎች መቸኮል ብሎ ነገር አልፈጠረባቸውም፤ ሁሉም በጊዜው ይሆናል ብለው ተረጋግተው ይጠብቃሉ።

እነዚህ ሰዎች ለውጫዊ ገፅታቸው ትኩረት የሚሰጡ በመሆኑ ደምቀው ለመታየት ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ።

ይህም ምንም እንኳን በፍጥነት ተስፋ የሚቆርጡ ባይሆኑም በራስ የመተማመን ብቃታቸው አነስተኛ መሆኑን ሊያሳይ እንደሚችል ነው የሚነገረው።

የሌሎች ሰዎችን አስተያየት እና ትችት የመቀበል ልማዳቸውም ትዝብት ውስጥ የሚከታቸው ነው ተብሏል።

 

 

 


ምንጭ፦ http://intellectunchained.com/

 

 

 

 

በፋሲካው ታደሰ