የስማርት ስልኮች ብርሃን በሰው ልጅ አንጎል ላይ ጉዳት የሚያደርሰው እንዴት ነው?

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ስማርት ስልኮች ለሰዎች የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በየቀኑ እያደገ ነው የመጣው።

በዚያው ልክም የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

አምራቾች የስማርት ስልኮች፣ የታብሌት እና የላፕቶፕ ስክሪኖች ከፍተኛ ብርሃን እንዲኖራቸው አድርገው ይሰራሉ፡፡

በስክሪኑ ላይ የሚጫነው የብርሃን አቅም በቀን ወይም በፀሃይ ወቅት ማየት እንዲቻል ሆኖ ነው የተሰራው፡፡

ሆኖም በጨለማ ሰዓት የብርሃን አቅሙ እጅግ ጠንካራ ይሆናል፡፡

የቴክኖሎጂ ውጤቶቹ የብርሃን መጠን በቀን ውስጥ በአንድ ትልቅ መስኮት ከሚገባ ጨረር ጋር እኩል ይሆናል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ምክንያት በምሽት ስማርት ስልኮችን መጠቀም አስቸጋሪ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተጠቁሟል፡፡

ሰውነታችን በቀን ውስጥ ንቁ ሆነን እንድንቆይ የሚያደርግ ተፈጥሯዊ የኡደት ስርዓት አለው፡፡

ይህ የኡደት ቅደም ተከትል ምሽት ላይ አካላችን ማረፍ እንዳለበትም ያሳውቃል፡፡

ሆኖም ለመተኛት ዝግጁ በምንሆንበት ጊዜ የስማርት ስልክ፣ የታብሌት ወይም የላፕቶፕ ስክሪን ላይ ማፍጠጥ ተፈጥሯዊውን የመንቃት እና የመተኛት ኡደት ያዛባዋል፤ አንጎላችንም ከመደበኛው ስራው ይስተጓጎላል።

በጣም ደማቅ የሆነው የኤሌክትሮኒክ ውጤቶች ብርሃን ሰውነታችን በእንቅልፍ እንዲያርፍ የሚያግዘውን ሜላቶኒን ሆርሞን አንጎላችን እንዳያመነጭ ያደርገዋል፡፡

የስማርት ስልክ የብርሃን ጨረሮች ሜላቶኒን የማመንጨት ሂደትን በማዛባት የሰዎችን እንቅልፍ ያስተጓጉላሉ።

ይህ የእንቅልፍ መዛባት ደግሞ የአንጎልን ስራ በማወክ ለከፋ የጤና ጉዳት ይዳርጋል ነው የተባለው፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍም የስማርት ስልኮች መተግበሪያ አምራቾች programs like f.lux እና Apple's Night Shift mode የተባሉ መተግበሪያዎችን ፈጥረዋል፡፡

አፕል ናይት ሺፍት ሞድ መተግበሪያ በምሽት ወቅት ከስክሪን የሚወጣውን ሰማያዊ የብርሃን ጨረር ይቀንሳል፡፡

መተግበሪውን የተጠቀሙት በርካታ ሰዎችም በዓይናቸው ላይ ጉዳት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ይህ የብርሃን መቀነሻ የእንቅልፍ መዛባትን ሊያስተካክል እንደሚችል ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡

ተመራማሪዎች የእንቅልፍ መዛባትን እና የአንጎል መታወክን ለማስተካከል የእንቅልፍ ሰዓት ሲደርስ ስማርት ስልኮችን አለመጠቀምን መክረዋል፡፡

ምንጭ፡-www.businessinsider.com