ለልብ ህመም መጋለጥዎን የሚያሳዩ ምልክቶች

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የህክምና ባለሙያዎች ሰውነት ላይ የሚታዩ ምልክቶችና ስሜቶች የራሳቸው መልዕክት እንዳላቸው ይናገራሉ።

በየጊዜው የጤንነትን ሁኔታ መከታተል እንደሚገባም ይገልጻሉ።

ይህም ሰውነት የተለየ ስሜት ባይታይበትም እንኳን የጤና እክል ተከስቶ ሊሆን ስለሚችል ችግሩን ለማወቅ ይረዳል ይላሉ።

እንደ ባለሙያዎች ገለጻ ከዚህ በታች ያሉት ምልክቶች ደግሞ የልብ ህመም ተጋላጭነትን የሚያሳዩ ናቸው።

የእንቅልፍ መቆራረጥ፦ አሁንም አሁንም መንቃትና መባነን ከልብ ህመም ጋር ታያያዥነት እንዳለው ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ።

የልብ ህመም ተጋላጭ ሲሆኑ የተቆራረጠ እንቅልፍ ይኖርዎታል፥ በአግባቡ መተኛትም አይችሉም።

ከዚህ ባለፈም የውሃ መጥማት ስሜት ካለም ይህ ችግር ተከስቶ ሊሆን ስለሚችል ወደ ህክምና ተቋም በማምራት ባለሙያን ያናግሩ።

ከፍተኛ ድካም፦ ስራ ሰርተውና ተንቀሳቅሰው እስከመጡ ድረስ የድካም ስሜት መከሰቱ አይቀርም።

ከዚህ በተቃራኒው ሆኖ ግን ከልክ በላይ የሆነ ድካምና ዘወትር ሰውነትዎ የመድከም ስሜት የሚያሳይ ከሆነ ወደ ህክምና ተቋም ያምሩ።

የእጅ መክበድ ስሜት፦ ከወትሮው የተለየ የእጅ መክበድ ስሜት እና እጅዎ እንደወፈረ ተሰምቶዎት ያውቃል?

እንዲያ ከተሰማዎት ልብን ከእጅና ከተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ጋር በሚያገናኘው ነርቭ አማካኝነት የደረሰዎት መልዕክት ነው።

መልዕክቱ ደግሞ ልብዎ ስራውን ለመስራት የሚያስችለውን በቂ ኦክስጅን አላገኘምና መላ ይፈልጉ ነው።
እናም እንዲህ አይነት ስሜት ሲሰማዎት በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም በማምራት ሃኪም ማማከርና መፍትሄ መውሰድ ይበጃል።

ጭንቀትና የምግብ አለመፈጨት፦ ለመጨነቅ ቀጠሮ ባያስፈልግም ይህ ስሜት እየበዛና እየጨመረ ከመጣ ግን ለምን ብለው መጠየቅ ይኖርብዎታል።

ከዚህ በተጨማሪም የምግብ አለመፈጨትና የሆድ አካባቢ የማቃጠል ስሜት ከተሰማዎትም መልዕክቱ ከልብ ህመም ጋር የተያያዘ ስለሚሆን ችላ አይበሉት።

የትንፋሽ መቆራረጥ፦ ልብዎ በቂ ኦክስጅን ካልደረሰው በጣም የመጨነቅና ትንፋሽ የማጣት እንዲሁም የትንፋሽ መቆራረጥ ችግር ይከሰታል።

ይህ ደግሞ ከልብ ህመም ጋር የተያያዘ ችግር ስለመከሰቱ ማሳያ ነውና ባለሙያ ያማክሩ።

እነዚህ የልብ ህመምና ተያያዥ ችግሮች ሊሰከቱ እንደሚችሉና በችግሩ እንደተጠቁ የሚያሳዩ ምልክቶች ስለሚሆኑ ባለሙያ ማማከርን ቀዳሚ ምርጫዎ ያድርጉ።

ከዚህ ባለፈ ግን የልብ ህመም ተጋላጭነትን ጤነኛ አመጋገብ በመመገብ መቀነስና ማስወገድ ይቻላልና አመጋገብዎን ያስተካክሉ።

የቅባትና ፋት መጠናቸው ዝቅ ያሉ ምግቦችን እንዲሁም በሶዲየም የበለጸጉ ምግቦችን ገበታዎ ላይ ማዘውተር።

በአሰር (ፋይበር) የበለጸጉ ምግቦችን፣ የአሳ ተዋጽኦዎችን፣ ጥራጥሬዎችን እንዲሁም ሳይበዛ ለውዝ መመገብ መልካም ነው።

ከዚህ ባለፈም እንደ ሩጫና መሰል ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በመከወን ራስዎን ይጠብቁ።

 

 


ምንጭ፦ ቢዝነስ ኢንሳይደር