ተመራማሪዎች ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት አይነ ስውርነትን መካላከል ችለናል አሉ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተመራማሪዎች ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣን አይነ ሰውርነት ለማስቆም የሚያስችል አዲስ ህክምና አግኝተናል ብለዋል።

የጆን ሆፕኪንስ ተመራማሪዎች ያገኙት አዲሱ የመከላከያ መንገድም ውጤታማ ነው የተባለ ሲሆን፥ ለበርካቶችም ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።

ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የአይን እይታ መጋረድ ለአይነ ስውርነት በመንስኤነት ከተዘረዘሩት በቀዳሚነት ተቀምጧል።

በአሜሪካ ብቻ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ሰዎች ከእድሜ ጋር ተያይዞ በሚከሰት አይነ ስውርነት ተጋልጠዋል።

የዚህ ችግር ተጠቂዎች አይነ ስውርነትን ለማከም በአይናችን “ማኩላ” ውስጥ የሚገኘውን ፈሳሽ በመቀነስ እይታን ለማሻሸል የሚረዳ “ቴራፒዩቲክ ፕሮቲን” መርፌ መውጋት የግድ ነበር።

የህክምና ሂደቱ ምቾት የሚነሳ እና ህመም ያለው በመሆኑን በርካታ የችግሩ ተጠቂዎች ህክምናውን ለማቋረት ሲገደዱ ተመልክተናል የሚሉት ተመራማሪዎች፤ ህክምናውን የሚያቋርጡ ሰዎች ብቸኛ አማራጭ ደግሞ አይነ ስውርነት ነው ይላሉ።

ታዲያ ይህንን ህክምና የሚተካ አዲስ መፍትሄ ይዘን መጥተናል የሚሉት ተመራማሪዎች፥ አዲሱ ግኝትም የፕሮቲን መርፌን ከመወጋት የተለየ ነው ብለዋል።

ይህም አይንን በቫይረስ መውጋት ነው ያለሉ ሲሆን፥ የቫይረሱ አይነትም ከጉንፋን ጋር ተመሳሳይነት ያለው እና በሰዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተደርጎ የሚዘጋጅ መሆኑን ገልጸዋል።

ቫይረሶቹም አንድ ላይ በመከማቸት የሬቲና ህዋሶች ፕሮቲን እንዲያመነጭ የሚረዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም አይናችንን ወደ ፕሮቲን ማምረቻነት በመቀየር ከዚህ ቀደም ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት አይነ ስውርነትን ለመከላከል ይሰጥ የነበረውን ተደጋጋሚ የፕሮቲን መርፌ መወጋትን የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል።

ህክምናውም ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት አይነ ስውርነትን ማከም እና ከመከሰቱ በፊት መግባት የሚችል መሆኑን ነው ተመራማሪዎቹ ያብራሩት።

ይህም ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን አይነ ስውርነት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ ውጤት እና ተስፋ የተጣለበት ስሜት መሆኑ ተነግሯል።

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.co.uk