ለስላሳና ቢራ በማቆም በቀን 1 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ውፍረትን በ20 በመቶ ይቀንሳል - ጥናት

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በየቀኑ አልኮል እና የለስላሳ መጠጦችን በማቆም አንድ ብርጭቆ ውሃን መጠጣት ከመጠን ያለፈ ውፍረትን በ20 በመቶ እንደሚቀንስ አንድ ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

የአውሮፓ ህብረት በፖርቹጋል ባካሄደው ከመጠን ያለፈ ውፍረት ጉባኤ ላይ የቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው፥ ሰዎች በየቀኑ የሚጠጡትን የለስላሳና የአልኮል መጠጥ በማስቀረት ውሃን ቢጠቀሙ ከመጠን ያለፈ ክብደታቸውን ማስተካከል እንደሚችሉ ይገልጻል፡፡

በተለይም በአንድ ጠርሙስ ቢራ ውስጥ 142 ካሎሪ፣ በ200 ሚሊ ሊትር ለስላሳ ውስጥ ደግሞ 78 ካሎሪ የሚገኝ በመሆኑ፥ ሰዎች ይህን መጠቀማቸው ለውፍረት እንደሚዳርጋቸው በጥናቱ ተነስቷል፡፡

one_glass_beer.jpg

ጥናቱ በ16 ሺህ ሰዎች ላይ ለአራት ዓመታት የተደረገ ሲሆን በየቀኑ ከለስላሳ እና ከቢራ መጠጦች በመራቅ አንድ ብርጭቆ ውሃን የሚጠጡት የውፍረት መጠናቸውን በአንድ አምስተኛ ቀንሰው ተገኝተዋል፡፡

በተለይም በየቀኑ ልንጠጣው የምንችለውን ባለ200 ሚሊ ሊትር ለስላሳ በማስቀረት ውሃ የምንጠጣ ከሆነ ውፍረን በ15 በመቶ መቀነስ ይቻላል፡፡

one_glass_water.jpg

የስፔኑ ናቫራ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጥናቱ ውስጥ ውፍረት ሊጨምሩ እና ሊቀንሱ የሚችሉ ሌሎች ነገሮችንም ከግንዛቤ ውስጥ አስገብተዋል፡፡

በጥናቱ ውስጥ ለውጥ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ታስበው የተካተቱ ነገሮችም የቤተሰብ የውፍረት ዳራ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና አመጋገብ ናቸው።

ሆኖም ከአመጋገብ አኳያ በወይን፣ የፍራፍሬ ጭማቂ፣ ቡና እና ወተትን ጨምሮ በሌሎች 15 መጠጦች ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊገኝ እንዳልቻለ ነው የተጠቀሰው።

አልኮል በይዘቱ ባለ ብዙ ካሎሪ በመሆኑ አልኮል የሚጠጡ ሰዎች ለከፍተኛ ውፍረት እና ከመጠን ላለፈ ክብደት ይዳርጋል።

በመሆኑም በየቀኑ ከአልኮል እና ከለስላሳ መጠጥ ይልቅ ቢያንስ አንድ ብርጭቆ ውሃን መጠጣት ተገቢ ነው ተብሏል፡፡

 

 

 

 

 

ምንጭ፡- ዴይሊ ሜይል