በዓለም ዙሪያ በታዳጊዎች ላይ ከሚከሰት ሞት የትራፊክ አደጋ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በዓለም ዙሪያ በታዳጊዎች ላይ ከሚከሰት ሞት ውስጥ የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዝ የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጣር በ2015 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ታዳጊዎች ይህወታቸው ያለፈ ሲሆን፥ ከዚህም ከ10 ታዳጊዎች ሞት ውስጥ አንዱ መንገድ ላይ ከሚከሰት የትራፊክ አደጋ ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው የተነገረው።

በመንገድ ላይ ለሚደርሱ አደጋዎች በብዛት የተጋለጡት ደግሞ እድሜያቸው ከ10 እስከ 19 ዓመት መካከል ያሉ ታዳጊ ወጣት ወንዶች መሆናቸውም ተገልጿል።

በታዳጊ እና ወጣት ሴቶች ላይ ከሚከሰት ሞት ደግሞ በደረት አካባቢ የሚያጋጥም ህመም እና ራስን መጉዳት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛልም ተብሏል።

እድሜያቸው ከ10 እስከ 19 መካከል ያሉ ታዳጊ ወጣቶችን ለሞት የሚዳርጉ 5 ምክንያቶች፦

1ኛ የመንገድ ላይ አደጋ

2ኛ ከመተንፈሻ አካል ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም የጤና እክል

3ኛ ራስን መጉዳት (ሆንብሎ እና በድንገት ራስን ማጥፋት)

4ኛ ተቅማት እና ትውከት

5ኛ ውሃ ውስጥ መስጠም

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በየእለቱ 3 ሺህ ታዳጊ ወጣቶች ህይወት ያልፋል።

በዓለም ላይ ከሚከሰተው የታዳጊዎች ሞት ውስጥ ደግሞ ሁለት ሶስተኛው ዝቅተኛ እንዲሁም መካከለኛ ገቢ ባላቸው የአፍሪካ እና ምስራቅ ኢሲያ ሀገራት ነው።

በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ከሚከሰቱት ውስጥ አብዛኛውን መከላከል የሚቻል መሆኑም ነውየተነገረው።

የመንገድ ላይ (የትራፊክ) አደጋ

በዓለም ዙሪያ አብዛኛው ታዳጊዎች እና ወጣቶች በመንገድ ላይ በሚከሰት የትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ እግረኞች፣ የብስክሌት እና የሞተር ሳይክል ተጠቃሚዎች የበለጠ ለሞት ተጋላጭ ናቸው ተብሏል።

road_accident_2.jpg

እድሜያቸው ከ15 እስከ 19 የሆኑ ታዳጊ ወንዶች በመንገድ ላይ ከሚከሰተው 115 ሺህ 302 አደጋዎች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙም ነው የተነገረው።

የእንግሊዝ ተመራማሪዎች እንደሚያብራሩት፥ ልጆች ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ወደ ሁለተኛ ትምህር ተሸጋግረው ብቻቸውን ወደ ትምህር ቤት መሄድ የሚጀምሩበት ጊዜ በጣም ለአደጋ የተጋለጠ ነው።

የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርትን የጻፉት ዶክተር አንቶኒ ካስቴሎ፥ በአንዳንድ ሀገራት ያለው የትራፊክ ደህንነት ትምህርት እና አስተዳደር አሽከርካሪዎች ፍጥነታቸውን እንዲቀንሱ የሚያበረታታ ነው፤ ይህ ደግሞ በመንገድ ላይ የሚከሰተውን አደጋ ይቀንሳል ይላሉ።

ሆኖም ግን አብዛኛው ሀገራት በዚህ ረገድ ብዙ ወደ ኋላ ቀርተዋል፤ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ዶክተር ኮስቴሎ ይመክራሉ።

ሌሎች ለታዳጊ ወጣቶች ሞት መንስኤ የሆኑ ነገሮች

በዓለም አቀፍ ደረጃ በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚከሰተው የሞት መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ሆኖም ግን አንዳንድ የሞት ምክንያቶች በብዛት ተመሳሳይ እየሆኑ መጥተዋል፤ ከነዚህም ውስጥ ራስን በራስ መጉዳት (ራስን ማጥፋት) አንዱ ሲሆን፥ በበርካታ አካባቢዎች እየተበራከተ መምጣቱን ነው ዶክተር ኮስቴሎ የሚናገሩት።

በተለይም ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም እየጨመረ መምጣቱንም ነው ዶክተሩ የሚያብራሩት።

ለዚህ ምክንያቱ ከፍተኛ ድብርት ነው፤ ታዳጊ ወጣቶች ደግሞ ከማንም በላይ ለድብርት ሊጋለጡ ስለሚችሉ ይህንን ለማስቀረት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል ባይ ናቸው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

በሙለታ መንገሻ