ልጆች ጥሩ ተግባቦትን እንዲፈጥሩ ለማድረግ ከወላጆችና ከሞግዚቶች የሚጠበቁ ተግባራት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እናት እና አባት ወይም የህጻናት ተንከባካቢዎች ልጆች እንዲያወሯቸው፣ የወደፊት ተስፋቸውን እና ምኞታቸውን እንዲያጋሯቸው ይፈልጋሉ፡፡

ታዲያ ወላጆች ልጆቻቸው ጥሩ የሃሳብ መጋራትን እንዲፈጥሩ መቼ እና እንዴት ምን ማድረግ አለባቸው ስለሚለው ጉዳይ፥ የማህበራዊ እና የስነልቦና ባለሙያዎች ሀሳባቸውን ያጋራሉ፡፡

ልጆች በጨቅላነታቸውም የመግባባት እና የመልዕክት ልውውጥ የመፍጠር ጉጉት አላቸው፡፡

በመሆኑም ወላጆች ይህን የልጆችን ፍላጎት በማየት ለተግባቦታቸው መቀላጠፍ፥ የበኩላቸውን ከፍተኛ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ የማህበራዊ እና የስነልቦና ዘርፍ ምሁራን ይመክራሉ፡፡

በመሆኑም ከልጆች ጋር ፊት ለፊት ግንኙነት በማድረግ የሚፈልጉትን ማሟላትና የሚጠይቁትን መመለስ ጠቃሚ ነው፡፡

ለልጆች ፈገግታን ማሳየት፣ ዜማዎችን ማዜም እና ማውራትም ከወላጆቹ ይጠበቃል፡፡

ህጻናት የሚያሳዩትን የፊት ገፅታ መቀበል እና በትህትና እያባበሉ ቃላትን ተጠቅሞ ምላሽ መስጠት፣ በኮልታፋ አንደበታቸው እንዲናገሩ ማበረታታት ይገባል፡፡

እነዚህን ተግባራት ማከናወን በልጆች እና በወላጅ ወይም በተንከባካቢዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባሻገር፥ ህጻናቱ የማህበራዊ እና የቋንቋ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ ያግዛቸዋል፡፡

እድሜያቸው ለቅድመ ትምህርት ሲደርስም ተረቶችን ማንበብ፣ ዜማዎችን በአንድ ላይ መዘመር፣ ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ መመለስ እና ሃሳባቸውን እንዲያጋሩን ማበረታታትም መልካም ነው ተብሏል፡፡

በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የልጆች የቋንቋ ክህሎት ሂደት ላይ በተደረገ ጥናት፥ ወላጆች ወይም ተንከባካቢዎቻቸው ልጆች መናገር የፈለጉትን ተረድተው ተገቢ ምላሽ ሲሰጧቸው የቋንቋ ችሎታቸው በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ይላል፡፡

ሆኖም ህጻናቱ የሚናገሩትን ነገር "እንደዚህ ነው የሚባለው" እያሉ ለማስተካከል እና እንደተሳሳቱ ለመናገር መሞከር ተገቢ አለመሆኑም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡

በደንብ የሚያዳምጧቸውን ተንከባካቢዎች ወይም ወላጆች ያገኙ ህጻናት፥ ችግር ቢያጋጥማቸው እንኳ እንደሚፈታ ያስባሉ፣ ለሕይወታቸውም ዋጋ እንደተሰጣቸው ይገምታሉ፡፡

እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እና ትምህርት ሲጀምሩም፥ ማህበራዊ ሕይወታቸው የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን እና ጥሩ ተግባቦትን እንዲያዳብሩ ቤተሰብ ሚናውን ሊጫወት ይገባል፡፡

ከጓደኞቻቸው ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ፣ ያለመሸማቀቅ እንዲያወሩ፣ እና ለሰዎች ታዛዥ እንዲሆኑ ወላጆች በቤታቸው ይህን ሁሉ ሂደት ማስለመድ ይኖርባቸዋል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ልጆች መልካም ማህበራዊ ተግባቦትን መፍጠር እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ያነሳሉ፡፡

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፡-www.telegraph.co.uk