በእግር መጓዝና ብስክሌት መጠቀም የልብና የካንሰር ህመም ተጋላጭነትን ይቀንሳል- ጥናት

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 12፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ረጅም እድሜ መኖር፤ የካንሰር ተጋላጭነትን መቀነስ እና የልብዎን ጤንነት መጠበቅ ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ ወደ ስራ ሲሄዱ ትራንስፖርት ከመጠቀም ይልቅ በእግር መጓዝን አሊያም ብስክሌትን ምረጡ ይሉናል ተመራማሪዎች።

ተመራማሪዎቹ ይህንን ያሉት ባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ የሆነውን ብስክሌትን መጠቀም እና በእግር መጓዝ ለልብ ጤንነት እና የካንሰር ተጋላጭነትን ከመቀነስ አንጻር ያለውን ጠቀሜታ ለመለየት ባደረጉት ትልቅ ጥናት ነው።

አምስት ዓመታትን የፈጀው ጥናት በ25 ሺህ እንግሊዛውያን ላይ የተካሄደ ሲሆን፥ በጥናቱም ወደ ስራ በሚሄዱበት ጊዜ የህዝብ ትራንስፖርትም ይሁን የግላቸውን ተሽከርካሪ ከሚጠቀሙት ይልቅ እግረኞች እና በብስክሌት የሚጓዙት የበለጠ ጤናማ ናቸው ተብሏል።

ጥናቱ በመካሄድ ላይ እያለ 2 ሺህ 430 ሰዎች ህይወት ያለፈ ሲሆን፥ 3 ሺህ 748 ሰዎች ካንሰር እንዳለባቸው ተለይቷል።

ከዚህ በተጨማሪም 1 ሺህ 110 ሰዎች ደግሞ የልብ ጤንነት ችግር መጋለጣቸው ታውቋል።

ሆኖም ግን በጥናቱ በየእለቱ ሳይክል መንዳት የመሞት እድልን በ41 በመቶ፤ የካንሰር ተጋላጭነትን በ45 በመቶ እንዲሁም የልብ ህመም ተጋላጭነትን በ46 በመቶ እንደሚቀንስ ተለይቷል።

እንዲሁም የእግር ጉዞ ማድረግ የልብ እና የሌሎች የጤና ችግር ተጋላጭነትን የሚቀንስ ሲሆን፥ በሳምንት በአማካኝ እስከ 10 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው የሚለው በጥናቱ ላይ ተቀምጧል።

ጥናቱን ካካሄዱት ውስጥ አንዱ የሆኑት ዶክተር ጄሰን ጊል፥ ይህ የእለት ተእለት ኑሯቸውን ንቁ ሆነው በእንቅስቃሴ የሚያሳልፉ ሰዎች ለጤንነታቸው ጠቀሜታን እያተፈሩ ስለመሆኑ ግልፅ ምስክር ነው ብለዋል።

በየእለቱ ወደ ስራ መሄድ ግዴታችን ነው፤ ታዲያ በዚህ ጊዜ ጉዞዋችንን በብስክሌት አሊያም በእግር የምናደርግ ከሆነ ሁሌም ለጤንነታችን አንድ ነገር አተረፍን ማለት ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው ሀገራት መሰረተ ልማቶቻቸውን ማስተካከል ነው፤ ይህም የብስክሌት መስመሮችን ማዘጋጀት እና መንገዶች ለእግር ጉዞ አመቺ እንዲሆኑ አድርጎ መስራት ይላሉ ዶክተር ጊል።

ምንጭ፦ www.bbc.com