ጨዋማ ምግቦችን መመገብ የርሃብ ስሜት እንጅ የውሃ ጥም እንደማይፈጥር ተመራማሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 11፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጨዋማ ምግቦችን መመገብ የርሃብ ስሜትን ይጨምራል እንጅ የውሃ መጠማት ስሜትን እንደማያመጣ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ

የርሃብ ስሜቱ የሚጨጀምረውም ሰውነታችን ብዙ የሃይል ፍላጎት ስላለው ነው ብሏል፤ በተለምዶ ጨዋማ ምግብን መመገብ ውሃ ውሃ ያሰኛል ይባላል፡፡

ሆኖም የስርዓተ ምግብ ባለሙያዎች ይህን ተለምዷዊ አተያይ ውድቅ የሚያደርግ ሀሳብ ይዘው ቀርበዋል፡፡

ወደ ማርስ በሚደረግ ጉዞ ላይ ጨዋማ ምግብን የሚጠቀሙ ተመራማሪዎች በሰውነታቸው ውስጥ በርካታ ውሃ እንደሚኖር እና ሰውነታቸው ተጨማሪ ሃይል ስለሚፈልግ ከጥማት ይልቅ ርሃብ እንደሚሰማቸው ነው ዓለም አቀፋዊ ጥናቱ የመሰከረው፡፡

 ጥናቱ ብዙ ጊዜ ጨዋማ ምግብ የሚመገቡ ሰዎች ብዙ የሽንት መጠን እንደሚኖራቸውም ጠቅሷል፡፡

የጀርመን የጠፈር ምርምር ማዕከል ተመራማሪዎች፣ የማክስ ዴልብሩክ የሞለኪዩላር ህክምና ማዕከል፣ የቫንደርቢት ዪኒቨርሲቲን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎች በጋራ ጥናቱን ሰርተዋል፡፡

በጥናቱም በጎ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች እንዲሳተፉ የተደረገ ሲሆን በሁለት ቡድን ተከፍሎ ነው ጥናቱ የተሰራው፡፡

በዚህ መሰረት የመጀመሪያው ቡድን ለ105 ቀናት ክትትል ሲደረግበት ሁለተኛው ደግሞ ለ205 ቀናት ክትትል ተደርጎበታል፡፡

በክትትሉ ወቅት ሶስት ዓይነት የጨው ምጣኔ ያለው ተመሳሳይ ምግብን ለተሳታፊዎች እንዲመገቡ የተደረገ ሲሆን፥ ከቀናቱ ርዝማኔ ውጭ ሌላ ልዩነት አልተደረገም።

በዚህ መሰረት ብዙ ጨዋማ ያለው ምግብ የተመገቡት ተጠኝዎች ብዙ የሽንት መጠን ተገኝቶባቸዋል ይላል በጆርናል ኦፍ ክሊኒካል ኢንቨስቲጌሽን የሰፈረው የጥናቱ ግኝት፡፡

ይኸውም ጨው ሰዎች በኩላሊታቸው ውስጥ ብዙ ውሃን እንዲያስቀምጡ ስለሚያደርግ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ጨው በሽንት ውስጥ ሲቆይ ውሃውን ወደ ኩላሊት እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች ይመልሳል፡፡

ውሃ በሰውነት ውስጥ መኖሩ ኩላሊት ጡንቻዎች እና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎች በአግባቡ እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል ሲሉ የጥናቱ መሪ ዶክተር ናታሊያ ነራኮቫ ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

www.sciencedaily.com