የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለምን እናደርጋለን?

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በጤና ለመሰንበት እና ደህንነትን ለመጠበቅም ይረዳል።

የህክምና ባለሙያዎችም በተደጋጋሚ ጠቀሜታውን ይገልጻሉ፤ ከዚህ በታች ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቢያደርጉ የሚያገኟቸውን ጠቀሜታዎች ዘርዝረዋል። 

የሰውነት ክብደትን ለመቆጣጠር፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አላስፈላጊ የሰውነት ውፍረትን መቆጣጠር ይችላሉ።

በሰሩ ቁጥር በርካታ መጠን ያለው ካሎሪን ያቃጥላሉ ይህ ደግሞ በኮሊስትሮል እና በቅባት ክምችት ሰውነት ላይ የሚፈጠር አላስፈላጊ ውፍረትን ያስወግዳል።

በዚህ ሳቢያም ጤንነትዎን መታደግ ይችላሉ፤ ከቻሉ በቀን ለግማሽ ሰዓት ያክል እንቅስቃሴን በማድረግ ወደ እለት ስራዎ ይሰማሩ።

በሽታን ለመዋጋት፦ ከአመጋገብ እና ከእንቅስቃሴ እጥረት ስለሚመጣው የደም ግፊት በሽታ የሚጨነቁ ከሆነ ፕሮግራም በማውጣት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፥ የልብ እና ተያያዥ የጤና እክሎችን ለመከላከል፣ የጭንቅላት ውስጥ ደም መፍሰስ እንዳይከሰት፣ ራስን ከአይነት 2 የስኳር በሽታ ለመከላከል፣ ከድብርትና ጭንቀት ለመውጣት ይረዳል።

ከዚህ ባለፈም ለበርካታ የካንሰር በሽታዎች እንዳይጋለጡም ይረዳዎታል፤ በሰውነት መገጣጠሚያዎች ላይ የሚፈጠር የጤና እክልን ለመከላከልም ጠቀሜታ አለው።

መነቃቃትን ለመፍጠር፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግዎ አዕምሮ ሰውነትን ለማነቃቃት የሚረዳውን ኬሚካል እንዲያመነጭ ይረዳዋል።

ይህ መሆኑ ደግሞ የመጫጫንና አላስፈላጊ የመፍዘዝ ስሜትን ለማስወገድ እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከዚህ ባለፈም በራስ የመተማመን መንፈስን በማጎልበት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ አጋዥ ይሆንለወታል።

ጥንካሬን ለማግኘት፦ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባደረጉ ቁጥር የሰውነት ጡንቻዎ መዳበርና መጠንከራቸው አይቀርም፥ ይህ ደግሞ ለሰውነት ብርታትና ጥንካሬን ያላብሳል።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለልብ ስራና ለደም ዝውውር የሚረዳው ኦክስጅንና ንጥረ ነገሮችን ሰውነት እንዲያገኝ ያደርገዋል።

የልብና የሳንባ ጤንነት ሲረጋገጥ ደግሞ የተሻለ ጥንካሬና ብርታትን ያገኛሉ ማለት ነው።

በቂ እንቅልፍ ለማግኘት፦ በእንቅልፍ መቆራረጥ የሚቸገሩና አሁንም አሁንም የሚነቁ ከሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግን ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ምክንያቱም ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ካደረጉ በኋላ ሰውነትዎ ነጻነትን ስለሚያገኝ በፍጥነት መተኛት ያስችልዎታል፤ በተቻለ መጠን በመኝታ ሰዓት አቅራቢያ እንቅስቃሴ አያድርጉ።

ማህበራዊ ህይዎትን ለማጣፈጥ፦ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ዘና በማድረግ የደስታ ስሜትን ይፈጥራል።

ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በሚያደርጉባቸው አካባቢዎች በሚያገኟቸው ነገሮችም ራስዎን ከሌሎች ነገሮች ጋር የሚያላምዱበትን እድል ይፈጥራሉ።

ይህ ደግሞ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንዲቀራረቡ በማድረግ ማህበራዊ ህይዎትዎን ሰፋ ባለ መንገድ እንዲመሩም ያስችልዎታል።

ጤንነትዎን ጠብቀውና በእንቅስቃሴዎ ዘና ብለው ለማትረፍ በሳምንት እስከ 150 ደቂቃዎችን መካከለኛ በሚባል ደረጃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያካሂዱ።

አልያም ለ75 ደቂቃዎች ከባድ እንቅስቃሴዎችን በሳምንት ውስጥ ይከውኑ።

ሩጫ፣ ብስክሌት ማሽከርከር፣ በእግር ለደቂቃዎች ሽርሽር ማድረግ፣፣ ዋና እና የጅምናዚየም እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉ ያተርፋሉና ይጠቀሙባቸው።

ምንጭ፦ mayoclinic.org