አካላዊ እርጅናን ለመከላከል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአካልም ሆነ በመንፈስ ወጣት ሆኖ መቆየትና ቶሎ አለማርጀት የብዙሃኑ ምርጫ እንደሚሆን ይገመታል።

በዚህ ረገድ እድሜ ቢገፋም በአካልም ሆነ በአዕምሮ ወጣት ሆኖ ለመታየትና ለመቆየት፥ ጤነኛ የህይዎት ዘይቤ ከመከተል ውጭ ሳይንሱ የተለየ ነገር እንደሌለ ይገልጻል።

በእንግሊዝ ዱክ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ሂተር ዊትሰን ደግሞ በገጽታም ሆነ በአዕምሮ ረገድ ወጣት ሆኖ ለመቆየት የሚከተሉትን መንገዶች ይመክራሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፦ ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በገጽታም ሆነ በአዕምሮ ረገድ ወጣት ሆኖ ለመታየት ወሳኝ መሆናቸውን ያነሳሉ።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረጉ ጠንካራ እና የተስተካከለ አቋም እንዲይዙ ከማስቻሉም ባለፈ ጤንነትን በማስተካከል የሚፈለገውን ውጤት ያስገኛልም ይላሉ።

የልብ ህመም ተጋላጭነትን መቀነስ፣ የተስተካከለ እንቅልፍ እንዲኖር ማድረግ፣ ለማስታወስ ብቃት፣ የድብርትና ድካም ተጋላጭነትን መቀነስ፣ ለአጥነት ጥንካሬ እና ድንገት የሚከሰቱ ራስን የመሳትና መሰል አጋጣሚዎችን መቀነስም ያስችላል።

ይህ መሆኑ ደግሞ በአካልም ሆነ በአዕምሮ ረገድ ወጣት ሆኖ ለመዝለቅ ይረዳወታል ባይ ናቸው።

አመጋገብ

እርሳቸው ያነሱት ሌላው ጉዳይ ለሰውነትም ሆነ ለአዕምሮ ግንባታ የሚረዳ ጤነኛ አመጋገብን መከተልን ነው።

አትክትና ፍራፍሬ፦ ትኩስ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም የተለያዩ ጥራጥሬዎችን መመገብ ሰውነት ቶሎ እንዳይገረጅፍ እና ገጽታዎን የእርጅና ምልክት እንዳያጋጥመው ይረዳል።

ከዚህ ባለፈም ለሰውነት ገጽታ ማርጀት እና መዳከም ምክንያት የሆኑ እንደ ልብ ያሉ የጤና ችግሮችን ለመከላከልና ለማስወገድም ይረዳል።

ቅባት የበዛበት አመጋገብን መቀነስ፦ እንደ ቅቤ ያሉና በሰውነት ውስጥ የቅባት ክምችትን የሚያመጡ ምግቦችን መቀነስም ባለሙያዋ ያቀረቡት ምክረ ሃሳብ ነው።

ከዚያ ይልቅ ንጹህ የፓልም እና የአትክልት ዘይቶችን ለምግብ ማብሰያ መገልገል መልካም መሆኑን አንስተዋል።

አሳና ስራስሮች፦ ስጋ አፍቃሪና ወዳጅ ከሆኑ ይህን መሰሉን ልማድ በሳምንት ውስጥ ከአንድ ጊዜ በላይ ባይደጋግሙት ብለው ይመክራሉ።

በሳምንት ሁለት ቀናትን አሳ እና የአሳ ተዋጽኦወችን መመገብና ስጋን በዚህ መልኩ መተካትም መልካም ውጤት ይኖረዋል።

ከዚህ ባለፈም ቲማቲም፣ ካሮትና ድንች በሾርባም ሆነ በወጥ መልክ አዘጋጅቶ መመገብም ለዚህ ይረዳልና ያንን ያድርጉ ሲሉም ይመክራሉ።

ሌላው ደግሞ የኑሮ ዘይቤ ነው፤ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከተሉት የአኗኗር ዘይቤ ከመጠጥና መሰል ጎጅ ልማዶች የጸዳና የራቀም ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በየዕለቱ የሚጠጡና እንደ ሲጋራ አይነት ደባል ሱሶች ካለብዎት በጊዜ ሂደት ለመሰል ችግር መጋለጥዎ አይቀርም።

እናም መሰል ልማዶችን በሂደት ማቆም ከዚህ መሰሉ የህይዎት ዘይቤ መራቅ ይገባወታል።

ብቸኝነት፦ አብዝቶ ብቻን መሆን እና ጊዜን በብቸኝነት ማሳለፍ ብዙ ማሰብና መብሰልሰልን ያስከትላል።

ይህ ጉዳይ በጊዜ ሂደት ድብርትና ጭንቀትን ያስከትላል፤ ያ መሆኑ ደግሞ ለአዕምሮ መረበሽና በሂደት ለሰውነት ጉስቁልና ይዳርጋል።

ስለዚህም በተቻለ መጠን ከሰዎች አይራቁ፥ ቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድና ጓደኝዎችዎ ጋር ጊዜ አብሮ ማሳለፍና ሃሳብ መለዋወጥን ያጎልብቱ ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰሯ።

በተቻለ መጠን ብቸኛ እንዳይሆኑ መጣርና ከሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍንም ይልመዱ።

መሰል ነገሮች የሚከሰቱ ከሆነም ወደ ባለሙያዎች ጎራ ማለትና ሃሳብን በማጋራት ምክረ ሃሳብ መቀበል።

አልያም በአካባቢዎ ወደ ሚገኝና በሚያምኑበት የእምነት እና መሰል ተቋም ጎራ በማለት ግንኙነትን ማዳበርና ብቻን አለመሆን መልካም መሆኑን ያስረዳሉ።

እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ምክረ ሃሳቦች በመቀበል በጫናና እና ሌሎች ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች የሚፈጠረውን በገጽታም ሆነ በአካል የማርጀትን ችግር መቅረፍ ይችላሉ።

 


ምንጭ፦ www.webmd.com