የእስራኤሉ አስፔክት የዓለማችን ትንሹን የኤም.አር.አይ መሳሪያ ሰራ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የእስራኤሉ አስፔክት ኢሜጂንግ ኩባንያ በዓለማችን በመጠኑ አነስተኛ የሆነ የኤም.አር.አይ መሳሪያ መስራቱን አስታውቋል።

ኤም.አር አይ (ማግኔቲክ ሬዞናንስ ኤሜጅ) የተሽከርካሪ እና ሌሎች አደጋ በሚያጋጥመን ጊዜ በጀርባ፣ በአንገት እና ሌሎች አካላችን ላይ የሚሰማንን ህመም ለመለየት የሚረዳ መሳሪያ ነው።

መሳሪያው ማግኔቲክ ፊልድ እና የራዲዮ ሞገድን በመጠቀም የሰውነታችንን ውስጣዊ ክፍል ለይቶ ፎቶ የሚያነሳ ሲሆን፥ ይህም የጉዳቱን ቦታ እና መጠን ለይቶ ለማወቅ ይረዳል።

ታዲያ የእስራኤሉ አስፔክት ኢሜጂንግ ይህን መሳሪያ ከዚህ በፊት ከነበረው በመጠን አሳንሶ መስራቱን ያስታወቀ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ግን ተመሳሳይ አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው አስታውቋል።

ትልቁ (በብዛት የተለመደው) ኤም.አር.አይ

MRI_2.jpg

አሁን በጥቅም ላይ ያለው የኤም.አር.አይ መሳሪያ መጠኑ በጣም ትልቅ ሲሆን፥ የአንድ ክፍልን አብዛኛ ስፍራ የሚይዝ ነው።

ሰዎች በዚህ ማሽን ውስጥ ገብተው ምርመራ በሚያደርጉበት ጊዜ ማሽኑ ፎቶግራፉን ሲያነሳ የሚወጣው ድምጽ ታካሚዎችን እንዳይረብሽ አንዳንዴ ለታካሚዎች የጆሮ ማዳመጫ ሲሰጥም ይስተዋላል።

በመሳሪያ በመመርመር ላይ ያሉ ሰዎች መሳሪያው ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜም መንቀሳቀስ የማይፈቀድላቸው ሲሆን፥ ሞባይል ስልካቸውን መጠቀምም አይፈቀድላቸውም፤ ይህም መሳሪያው በሚያነሳው ምስል ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳያሳርፍ ነው።

አዲሱ ኤም.አር.አይ

MRI_3.jpg

የእስራኤሉ አስፔክት ኢሜጂንግ አሁን በጥቅም ላይ ያለውን የኤም.አር.አይ መሳሪያ አሰራርን የሚቀይር አዲስ ነገር አካቷል።

ኩባንያው መጠኑን አሳንሶ የሰራው የኤም.አር.አይ መሳሪያ በሙከራ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፥ እንደ ካንሰር ያሉ ህመሞች ላይ ጥናት በሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ውስጥም በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።

ምንጭ፦ www.techworm.net

በሙለታ መንገሻ 

android_ads__.jpg