የስኳር ፍጆታችን ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች..

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጣፋጭ ነገሮችን በተለይም ስኳር አብዝቶ መውሰድ በአጠቃላይ ጤናችን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው ተደጋግሞ ይነሳል።

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሰባት ነጥቦችም የስኳር ፍጆታችን ከፍተኛ መሆኑን ያሳያሉ ተብሏል።

1. አቅም ማጣት እና ከፍተኛ የድካም ስሜት

ስኳር አብዝተን መውሰዳችን ከሚያሳዩ ምልክቶች መካከል በተደጋጋሚ አቅም የማጣት እና የመዛል ስሜት ቀዳሚው ነው።

ከፍተኛ የስኳር ይዘት ያላቸው ምግቦች ጉልበት የመጨመር ባህሪ አላቸው፤ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜ ነው።

በመሆኑም በተደጋጋሚ የድካም ስሜት የሚሰማን ከሆኑ የስኳር አጠቃቀማችን መቀነስ እና አመጋገባችን ማስተካከል አለብን።

2. ተደጋጋሚ ጉንፋን

ከተለመደው ጊዜ በተለየ በተደጋጋሚ ለበሽታዎች መጋለጥም የስኳር አወሳሰዳችን መስመሩን መልቀቁ ማሳያ ነው።

ረዘም ላለ ጊዜ ስኳር አብዝተን የምንወስድ ከሆነ በሽታ የመከላከል አቅማችን ይዳከማል፤ በተለይም ጉንፋንን መቋቋም ይሳነናል።

በመሆኑም ለተለያዩ በሽታዎች ከመጋለጣችን በፊት የስኳር ፍጆታችንን ዞር ብሎ መመልከት ያስፈልጋል።

3. የአዕምሮ መዛል፤ በተለይም ከምግብ በኋላ

በደም ውስጥ የሚገኝ ስኳር መጠን መቀነስን ከሚያሳዩ ነገሮች መካከል የአዕምሮ መዛል ነው።

በሂደት በደማችን ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠንን ለማሳደግ ከምናደርገው ጥረት ይልቅ በተደጋጋሚ ስኳር አብዝተን መውሰድ የደም ስኳር በፍጥነት እንዲጨምር እና ወዲያውኑ እንዲቀንስ ያደርጋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት በደም ውስጥ የሚገኝ የስካር መጠንን በአግባቡ ለመቆጣጠር አለመሞከር ለአዕምሮ ጤና ችግር ይዳርጋል።

4. የማጣጣም ችሎታ መቀነስ

ስኳር አብዝቶ መውሰድ የማጣጣም ችሎታን ይነጥቃል፤ ከስኳር ውጭ የሚጣፍጥ ነገር የለም የሚል እሳቤ ውስጥም ይከታል።

ስኳር ያልበዛበት ሻይም ሆነ ቡና መጠጣት የማያረካን ከሆነም ቆም ብለን ማሰብ ይገባል ተብሏል።

በጊዜ ሂደት ደግሞ አንዳንድ አነስተኛ ስኳር ያላቸው ምግቦችም ሆኑ መጠጦች በጣም ጣፋጭ ሆነው ካገኘናቸው ችግር አለ ማለት ነው።

5. የቆዳ እና ፊት ገፅታ መቀየር

ስኳር ሰውነታችን ወይንም ቆዳችን እንዲቆጣ ሊያደርግ ይችላል። በቆዳ ላይ የሚወጡ ነጠብጣቦች፣ ሽፍታዎችና የቆዳ መቅላት፣ የቆዳ መድረቅ እንዲሁም ቅባታማ መሆንም የስኳር ፍጆታችን ከፍተኛ መሆኑን ያሳያሉ።

በርካታ የስኳር ፍጆታቸውን የቀነሱ ሰዎች ከቆዳቸው ጋር ተያይዞ ያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ እንዳስቻላቸው ይነገራል።

6. የክብደት መጨመር

ስኳር የፋይበር እና ፕሮቲን ይዘት የለውም። በመሆኑም ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር ስንመገብ ከፍተኛ ካሎሪ እናገኛለን ማለት ነው።

ስኳር የኢንሱሊን ሆርሞን መመረትን ያፋጥናል።

ከፍተኛ መጠን ያለው ስኳር መጠቀም ሰውነታችን በርካታ መጠን ያለው ኢንሱሊን እንዲያመርት በማድረግ ችግር ይፈጥራል።

የኢንሱሊን መጠንን መቆጣጠር ያለመቻል ችግርም ከልክ በላይ ውፍረት ጋር በቀጥታ ግንኙነት አለው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2010 በኮሎራዶ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በ4 ሺህ 500 ወጣቶች ላይ የተደረገ ጥናት ደግሞ የደም ግፊት ችግር እና ከፍተኛ የስኳር ፍጆታ ግንኙነት እንዳላቸው አረጋግጧል።

7. ፍርሃት እና ጭንቀት

ስኳር በተደጋጋሚ ከልክ በላይ መውሰድ ሰውነታችን ጥንካሬውን እንዲያጣ ያደርጋል፤ ይህም ስነልቦናዊ ጥንካሬያችን ይቀንሳል።

ጭንቀት እና ከማህበራዊ ግንኙነት መነጠልን መምረጥ የስኳር ሱሰኞች ባህሪ መሆኑም ይነገራል።

ፍርሃት፣ ንዴት እና የብቸኝነት ስሜትም የስኳር ይዘት የበዛበት አመጋገባችን እንድናስተካክል የሚጠቁሙ ቀይ መብራቶች ናቸው ተብሏል።


8. የጥርስ ህመም

በልጅነታችን ጣፋጭ ነገሮችን መመገብ ጥርሳችንን እንደሚያበላሽ እየተነገረን ያደግን እንኖራለን።

በእርግጥም ስኳር የበዛባቸውን ምግቦች መመገብ ለጥርስ ህመም በማጋለጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ጥናቶች አረጋግጠዋል።

9. የስኳር በሽታ

ስኳር እና ስኳር የበዛባቸው ምግቦችን ማዘውተር ከልክ ላለፈ ውፍረት ይዳርጋል፤ ከልክ በላይ ውፍረትም ለታይፕ 2 የስኳር በሽታ የማጋለጥ እድልን ይጨምራል።

በየተወሰነ ጊዜ ልዩነት ውሃ የሚጠማን እና የሚርበን ከሆነ ለስኳር በሽታ ተጋልጠን ሊሆን ስለሚችል ሀኪሞችን ማማከር ተገቢ ነው።

10. የልብ ችግሮች

ስኳር በልብ ጤና ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም።

በኬስ ሪሰርቭ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በአይጦች ላይ በተደረገ ምርምር፥ ስኳር የበዛባቸው ምግቦች ከፍተኛ ስብ እና ስታርች ከያዙ ምግቦች ይልቅ ለልብ ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራሉ።

በአጠቃላይ ማርም ሲበዛ ይመራል እንደሚባለው ሁሉም በልክ ይሁን! የዛሬው መልዕክታችን ነው።

በአጠቃላይ ማርም ሲበዛ ይመራል እንደሚባለው ሁሉም በልክ ይሁን! መልዕክታችን ነው።

 

 

ምንጭ፦ www.healthyandnaturalworld.com/

 

 


በፋሲካው ታደሰ