ቫይታሚን ቢ በአየር ብክለት የሚመጣን አካላዊ ጉዳት ይቀንሳል-ጥናት

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 6 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የአየር ብክለት በሰው ልጅ ጤና ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቫይታሚን ቢ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አንድ ዓለም አቀፋዊ ጥናት አሳየ፡፡

የአየር ብክለት በሰዎች ላይ በርካታ የጤና ጠንቆች ያመጣል፡፡

በሆንግ ኮንግ፣ በሃርቫርድ እና በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲዎች ጥምር ተመራማሪዎች የተሰራው ዓለም አቀፍ ጥናት በቫይታሚን ቢ ውጤቶች በብክለቱ የሚመጡ በሽታዎች በሰውነት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ያደርጓቸዋል፡፡

ሆኖም በብክለቱ የመጡ በሽታዎች ገና ለጋ በሆኑበት ወቅት እንጂ ከበሰሉ በኋላ ቫይታሚን ቢ ያስወግዳቸዋል ማለት እንዳልሆነም አስተምረዋል፡፡

በከባቢው ላይ በጭስ ወይም በአቧራነት የሚታዩት ጥቃቅን በካዮች አየሩ ላይ በሚያደርሱት ጉዳት ወደ መተንፈሻ አካላችን የተበከለ አየር እንዲገባ ያደርጋሉ፡፡

በሆንግ ኮንግ ከተማ ዩኒቨርሲቲ የከባቢያዊ ሁኔታ ፕሮፌሰሩ ቻክ ኬ ቻን እንደሚሉት፥ ጥቃቅን አቧራዎች በተበከለው አየር አማካይነት ወደ ሳንባችን የመግባት እድል አላቸው፡፡

ጥቃቅን በካዮቹ ወደ ሰውነታችን ከገቡ በኋላ በመተንፈሻ አካሎች ላይ ከፍተኛ የመታፈን እና የመቁሰል አደጋን ያደርሳሉ፤ ለጭንቀትም ይዳርጋሉ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፡፡

እንደ ዓለም ጤና ድርጅት 92 በመቶ የሚሆነው የዓለም ሰው የሚኖረው የተበከለ ከባቢ አየር ባለበት አካባቢ ነው፡፡

የእያንዳንዱ ግለሰብ የበሽታ መከላከል አቅም እና ግንዛቤ ያልዳበረ መሆኑ፥ የአየር መበከልን የሚያስከትሉ ጥቃቅን አካላት ወይም አቧራዎች ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ ያገዝፈዋል ያሉት ደግሞ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲኗ አንድሪያ ባካሬሊ ናቸው፡፡

ጥናቱ በቶሮንቶ ከተማ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የጥናቱ ተሳታፊዎች ለፊታቸው ማስክ ለብሰው የቫይታሚን ቢ ውጤቶችን ከተሰጡ በኋላ፥ በሰዓት 1 ሺህ ተሸከርካሪ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ለተበከለ አየር እንዲጋለጡ ተደረጉ፡፡

ከዚያም ለአራት ሳምንታት ጥናቱ ተሰርቶ በተደረገው ምርመራ የቫይታሚን ቢ አይነቶችን በየቀኑ መውሰድ የተበከለ አየር በሰውነታችን ውስጥ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ እንደሚቀንስ ተረጋግጧል፡፡

ይህም የሚያሳየው በሽታን ለመከላከል እያንዳንዱ ሰው የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ነው ብለዋል ተመራማሪዎቹ፡፡

ተመራማሪዎቹ የተበከለ አየር የሚያደርሰውን ጉዳት በቫይታሚን ቢ መቀነስ ቢቻልም፥ የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ ግን ዋነኛው ተልዕኮ ሊሆን ይገባዋል ሲሉ ባለ ጭስ ኢንዱስትሪዎችን አሳስበዋል፡፡

መንግስታትም ግለሰቦች ከተበከለ አየር ለመጠበቅ ከሚያደርጉት ተሳትፎ በላይ ዜጎቻቸው ንፁህ አየርን እንዲተነፍሱ፥ የከባቢ አየር ጥበቃ ፖሊሲዎቻቸውን እና ህጎቻቸውን ማጥበቅ ለተግባራዊነታቸውም በጋራ መረባረብ እንዳለባቸው ነው የተነገረው፡፡

 

 

 

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን