ኮምፒውተር ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም ህመምና መፍትሄው…

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 9፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አብዛኛውን ጊዜያችንን ኮምፒውተር ላይ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የምናሳልፍ ከሆነ ለተለያዩ ችግሮች ልንጋለጥ እንደምንችል በተለያየ ጊዜያት ተነግሯል።

በስራ ገበታችን ላይ ስንሆን አብዛኛውን ጊዜያችንን በኮምፒውተር ላይ የምናሳልፍ ከሆነና እንደ የራስ ምታት፣ የአይን መድረቅ፣ የማቃጠል እና ብዥታ ከተፈጠረ እንዲሁም የአንገት ህመም ከተሰማን “የኮምፒውተር እይታ ህመም ነው” ይሉናል ተመራማሪዎች።

እንዲህ አይነት ምልክቶች በቀን ውስጥ ከ3 ሰዓት በላይ ከኮምፒውተር ጋር የሚያሳልፉ ሰዎች ላይ ሊስተዋሉ እንደሚችሉም ነው የተነገረው።

በዓለም አቀፍ ደረጃም ከ70 ሚሊየን በላይ ሰዎች ለዚህ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን ጥናት የሚያሳይ ሲሆን፥ ይህ ችግር በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከፍተኛው የስራ ላይ እክል እየሆነ መጥቷል።

እድሜያቸው ከ11 እስከ 18 ዓመት በሆኑ 642 ኢራናዊያን ላይ በተሰራ ጥናት 70 በመቶ ያክሉ የጥናቱ ተሳታፊዎች በቀን ቢያንስ ለ2 ሰዓታት ያክል በኮምፒውተር ላይ ያሳልፋሉ።

ታዲያ አብዛኛው የጥናቱ ተሳታፊ አይናቸው ላይ የማቃጠል ችግር፣ እንዲሁም እይታቸው ላይ ብዥታ የመፈጠር ችግር፣ የአይን መድረቅ እንዲሁም ለራስ ምታት የተጋለጡ መሆናቸውም ተለይቷል።

በተለይም ችግሩ በቅርበትና በርቀት የማየት ችግር ባለባቸው ሰዎች ላይ እንደሚብስ የተነገረ ሲሆን፥ የተወሰኑት ከህመም ስሜቱ ለመላቀቅ ሰዓታት ብቻ የሚበቃቸው ቢሆንም፥ አብዛኞቹ ግን እስከ አንድ ቀን እንደሚፈጅባቸው ተነግሯል።

የኮምፒውተር እይታ ህመምን ለማከም…

1. በየ 20 ደቂቃ ልዩነት እረፍት ማድረግ

ከኮምፒውተር እይታ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የህመም ስሜትን ለማከም በየ 20 ደቂቃ ልዩነት ለ20 ሰከንድ አይናችንን ከኮምፒውተራችን ላይ በማንሳት እረፍት ማድረግ ይኖርብናል።

በዚህ ጊዜም በአካባቢያችን እስከ 6 ሜትር ርቀት ውስጥ የሚገኙ ነገሮች ላይ ማተኮር መልካም ነው።

2. አይናችንን ማርገብገብ

አብዛኛውን ጊዜ ከኮምፒውተር ስክሪን ጋር በምናሳልፍበት ጊዜ አይናችንን በመደበኛ ሰዓት ከምናርገበግብበት በታች ነው የምናርገበግበው።

ይህ ደግሞ አይናችን ተገቢውን እንቅስቃሴ ባለማድረጉ ለአይን ድርቀት እና ማቃጠል ለመሳሰሉት ችግሮች ሊዳርገን ይችላል።

ስለዚህ በኮምፒውተር ላይ አትኩረን ስራችንን በምንሰራበት ጊዜ በተቻለን መጠን አይናችንን ቶሎ ቶሎ ማርገብገብ ይኖርብናል።

3. መነፅር መጠቀም

በአሁኑ ጊዜ በብዛት ገበያውን የተቆጣጠሩት ፍላት የኮምፒውተር ስክሪኖች ብርሃን መቀነሻ ተጨማሪ መስታወት ያልተሰራላቸው በመሆኑ ከኮምፒውተሩ ላይ የሚመጣው ጨረር ቀጥታ

ከአይናችን ጋር በመገናኘት አይናችን ላይ ጉዳት ሊያስከትልብን ይችላል።

ስለዚሀም ባለሙያ በማማከር ጨረር ሊከላከሉን የሚችሉ መነፅሮችን መጠቀምም ይመከራል።

4. በኛ እና በኮምፒውተራችን መካከል ርቀት እንዲኖር ማድረግ

ስራችንን በምንሰራበት ጊዜ በእኛ እና በኮምፒውተራችን መካከል ያለው ርቀት ለጤናችን ወሳኝነት አለው።

በተለይም ኮምፒውተሩን ከአይናችን ትይዩ ዝቅ አድርገን መስራት ምቾት እንዳለው ነው የሚነገረው።

ስለዚህም ኮምፒውተራችን ከአይናችን ትይዩ ከ10 እስከ 15 ሴንቲ ሜትር ዝቅ ብሎ እንዲቀመጥ ማድረግ መልካም ነው።

እንዲሁም በኮምፒውተራችን እና በፊታችን መካከል ያለው ርቀት ደግሞ ከ46 እስከ 66 ሴንቲ ሜትር ርቀት እንዲኖር ይመከራል።

የጀርባ ህመም፣ በጭንቀት የሚከሰት የራስ ምታት እና ምቾት ማጣት በኮምፒውተር ስክሪን አማካኝነት የሚከሰት ስላልሆነ አካባቢያችንን ለስራችን እንዲመች ማድረግ ይኖርብናል።

ምንጭ፦ www.theguardian.com


በሙለታ መንገሻ

android_ads__.jpg