በልጆቿ እንቅልፍ ማጣት ለሶስት ዓመታት በየዕለቱ 2 ሰዓት ብቻ የምትተኛው እናት እፎይ ብላለች

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 8፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሜልቦርን ነዋሪዋ ስካይ ቶክሂ በልጆቿ እንቅልፍ ማጣት ምክንያት ላለፉት ሶስት ዓመታት በቀን ውስጥ ሁለት ሰዓት ብቻን ለመተኛት ተገዳ ነበር፡፡

ይህቺ እናት የሶስት ዓመት እና የ9 ወር እድሜ ያላቸው ልጆች አሏት።

ስካይ ቶክሂ እንደምትለው፥ የሶስት ዓመት ልጇን አማያን እንቅልፍ እንዲወስዳት ለማድረግ ላለፉት ሶስት ዓመታት በየምሽቱ ብዙ ጥረት ብታደርግም፥ አማያ እንቅልፍ ከመተኛት ይልቅ አይኗን ፍጥጥ አድርጋ መቆየትን ከዚያም ሌሊት ላይ ተነስታ ማልቀስን ትመርጣለች፡፡

አማያ በነቃች እና ባለቀሰች ቁጥርም አባት እና እናት ምንም ማድረግ ባይችሉም፥ ከእንቅልፋቸው ተነስተው በማባበል እንቅልፏ እንዲመጣ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

በግል ጥረታቸው ለውጥ ያመጡት የአማያ እናት እና አባትም ያለማከሩት ሰው እና ያላነበቡት መጽሐፍ ባይኖርም እንቅልፏን የሚቀርፈው መፍትሔ ግን ቶሎ አልተገኘም፡፡

በዚህ ጊዜ ታዲያ ስካይ ቶክሂ እና ባለቤቷ የሶስት ዓመት ልጃቸውን እንቅልፍ የሚያስተኛ ከሆነ በሚል ሌላ ወንድም ወይም እህት ሊወልዱላት ወሰኑ፡፡

ከወራት በኋላም አማያ እህት ተወለደቺላት ስሟም ኢይላ ተባለች፤ ስሟንም ተስፋችንን የምታለመልም ናት በሚል እንዳወጡላት፣ ትርጉሙም የጨረቃ ብርሃን ማለት እንደሆነ ቶክሂ ተናግራለች፡፡

sleep_less2.jpg

ሆኖም የአማያ ታናሽ እህት ኢይላም እንደ ታላቅ እህቷ ሁሉ እንቅልፍ በአይኗ ሊዞር አልቻለም፡፡

እናት እና አባት ልጅ በመውለዳቸው ይደሰቱ እንጅ የእንቅልፍ ዕጦታቸውን ባለማስወገዳቸው የበለጠ ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ።

በተፈጠረው ችግርም ስካይ ቶክሂ ለጭንቀት እና ለከባድ ድብርት መጋለጧን ገልፃለች።

ከብዙ ድካም በኋላም ጭንቀታቸውን የሚያቀል መድህን ተገኘ፤ በሜልቦርን በሚገኝ ሚትቻም የተሰኘ የግል ሆስፒታል የእንቅልፍ ትምህርት ቤት ውስጥ ገብተው እንቅልፍ የሚያስተኛ እርዳታ በባለሙያዎቹ ተደረገላቸው፡፡

የእንቅልፍ ትምህርት ቤቱም የእንቅልፍ ማምጫ መንገዶችን እና እናቶች በራሳቸው መንገድ ልጆቻቸውን እንዴት መንከባከብ እንዳለባቸው የሚያሳውቅ ሳይንሳዊ ትምህርትን ስካይ ቶክሂን ጨምሮ ለበርካታ እናቶች ሰጥቷቸዋል፡፡

በዚህ የእንቅልፍ ትምህርት ቤት የመፍትሔ መንገድ፥ ኢይላ አስገራሚ ለውጥ በማሳየት በቀን ውስጥ ለ11 ሰዓታት መተኛት ስትችል፣ አማያ በበኩሏ መጠነኛም ቢሆን ለውጥ አምጥታለች፡፡

በዚህም እናት ስካይ ቶክሂ "አሁን ላይ ገነት ውስጥ ያለሁ ያህል ጭንቀቴ ተወግዶልኛል" ብላለች፡፡

"እንደ እናት ሆኖ ላየው፥ የልጆች የእንቅልፍ እጦት ስቃዩ ከባድ ነው፤ አካላዊም ሆነ አዕምሯዊ ጉዳትንም ያመጣል፤" የምትለው ቶክሂ፥ እናቶች ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥማቸው እርዳታን መፈለግ እንዳለባቸውና ወደ ባለሙያዎች መሄድ እንደሚኖርባቸው ተናግራለች፡፡

 

 

ምንጭ፡- ደይሊሜይል