ሳይርበን መብላት ከምናስበው በላይ ጉዳት እንዳለው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስንቶቻችን የርሃብ ስሜት ሲሰማን ብቻ ምግብ እንበላለን?

የቁርስ፣ የምሳ፣ የመክሰስ እና የእራት ሰዓት ጠብቆ መመገብ በአብዛኛው ህብረተሰብ ውስጥ ልማድ ሆኗል።

ምግብ ሲገኝ የርሃብ ስሜት ባይኖርም አሁንም አሁንም መብላት ሲታጣ ደግሞ ከረሃብ ስሜት አልፎ ሰውነት እስኪጎዳ ድረስ ፆምን መዋል እና ማደረም እንዲሁ ሌላው መገለጫችን ነው።

በተለምዶ ሳይርበን አብዝቶ ቶሎ ቶሎ መመገብ እና ከአቅም በላይ መብላት ለቁንጣን ይዳርጋል ይባላል፤ ከመጠን በላይ ለሆነ ውፍረት እና ክብደት እንደሚዳርግም ይነገራል።

ከዚህ ባሻገር ሳይርብ ምግብ መብላት ወይም በብዛት መመገብ ሌላም ጠንቅ አለው ሲል በቺካጎ የኢልኖይስ ዩኒቨርሲቲ ጥናትን ጠቅሶ ሳይኮሎጂ ቱደይ አስነብቧል፡፡

ይህም በደማችን ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን በእጅጉ በመጨመር የጤና ስርዓታችን ያዛባል።

ምግብ ወደ ሰውነታችን ባስገባን ቁጥር በርካታ የስኳር ይዘት ያላቸው ንጥረ ነገሮችን ወይም ካሎሪዎችን በሰውነታችን ውስጥ ስለሚዋሃዱ ነው ባገኘነው አጋጣሚ መመገብ ለጤናችን ጠንቅ ነው የተባለው።

ሰውነታችንም በጣፊያችን ውስጥ በሚገኙ አስወጋጅ ሆርሞኖች አማካኝነት የስኳር ንጥረ ነገሮችን የሰውነት የሃይል መጠን ሲቀንስ ለመጠቀሚያነት ከደም ዝውውር አስወጥቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡

በመደበኛው የደም ዝውውር ውስጥ በደማችን የሚገኘው ስኳር ከምግብ በኋላ የሚጨምር ሲሆን በጣፊያችን በሚገኙ አስወጋጅ ሆርሞኖች አማካኝነት ግን መጠኑ እጅግ ከፍ ይላል ነው ያለው ጥናቱ፤ በዚህም ለጤና ስጋት ይፈጥራል፡፡

በደማችን ውስጥ ካለው መደበኛ ስኳር መጠን ላይ ሌላ ተጨማሪ የስኳር መጠንን ቶሎ ቶሎ በምንመገበው ምግብ አማካኝነት ወደ ሰውነታችን ካስገባን ለበሽታዎች የመጋለጥ እድላችን የሰፋ ነው የሚሆነው፡፡

እስካሁን ድረስ የምንመገበው ምግብ የስኳር መጠን ተመሳሳይ መሆኑን እናስብ ይሆናል።

ሆኖም አመጋገባችን በጨመረ እና የምግብ መጠናችን በሰፋ ቁጥር የስኳር መጠናችን ይጨምራል፡፡

በቺካጎ የኢልኖይስ ዩኒቨርሲቲ ያጠናው ጥናት ሰዎች ሳይርባቸው በሚመገቡበት ሰዓት ጉዳት አምጪ የስኳር መጠንን ወደ ሰውነታቸው የሚስገቡት ሲርባቸው ከሚመገቡት የካሎሪ መጠን የበለጠ ይሆናል ብሏል።

ጥናቱ ብትችሉ እስኪርባችሁ ድረስ ከምግብ ራቁ፤ ሲርባችሁም የስኳር መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦችን ተመገቡ፤ ይህን ጊዜም ጣፊያችሁ "መጠነኛ ስኳር ስለላካችሁልኝ አመሰግናለሁ!" ይላችኋል ሲል መክሯል፡፡

 

ምንጭ፡- ሳይኮሎጂ ቱደይ

በምህረት አንዱዓለም

android_ads__.jpg