ለከፍተኛ የደም ግፊት የተጋለጡ ሰዎች ቁጥር አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ጨምሯል- ጥናት

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለም ዙሪያ በርካታ ሰዎች በከፍተኛ የደም ግፊት መጠቃታቸውን ከሰሞኑ የወጣ ጥናት አመልክቷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በ9 ሚሊየን ሰዎች ላይ የተደረገው ይህ ጥናት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1990 እስከ 2015 የደም ግፊት መጠን በምን ያክል ጨምሯል የሚለውን ነው ጥናቱ የተመለከተው።

በጥናቱ ላይ በመመርኮዝም በአሁኑ ጊዜ ምን ያክል ሰው ለደም ግፊት ተጋልጠዋል የሚለው ተለይቷል።

በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሽንግተን የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ክርስቶፈር ሙረይ፥ “በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ሰዎች ለከፍተኛ የደም ግፊት የተጋለጡ መሆናቸውን በጥናታችን መለየት ችለናል” ብለዋል።

ሙረይ አያይዘውም የደም ግፊት በአሁኑ ጊዜ ለበርካታ ሞት እና የአካል ጉዳት መንስኤ እየሆነ መምጣቱንም ገልጸዋል።

የደም ግፊት በሁለት ቁጥሮች ነው የሚለካው የተባለ ሲሆን፥ ከነዚህም አንዱ የላይኛው ወይም ሳይስቶሊክ ግፊት ይባላል፤ ይህ ደም ከልባችን ውስጥ በሚወጣበት ጊዜ በደም ስራችን ውስጥ ያለውን የደም መጠን የሚለካ ነው።

ሁለተኛው የታችኛው ቁጥር የሚባል ሲሆን፥ ዲያስቶሊክ ይባላል፤ ይህም በደም እና በልብ ምት መካከል ያለውን የግፊት መጠን የሚለካ ነው።
የደም ግፊት ልኬትም በሜርኩሪ ሚሊሜትር (mm Hg) ነው የሚለካው ተብሏል።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ፥ የሳይስቶሊክ የደም ግፊት መጠኑ መደበኛ በሚባለው ደረጃ ላይ ማለትም 120/80 ላይ ቢሆን እንኳ የልብ እና የስትሮክ ህመም ተጋላጭነትን ይጨምራል።

በጥናቱም የሳይስቶሊክ የደም ግፊት መጠን ከ110 እስከ 115 መካከል በሚሆንበት ጊዜ መጠነኛ ጭማሪን ያሳየ ነው ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን፥ የሳይስቶሊክ መጠኑ ወደ 140 ካደገ ግን ከፍተኛ የደም ግፊት ስለሚሆን ልብ ልንለው ይገባል ተብሏል።

የጥናት ቡድኑ መሪ ክርስቶፈር ሙረይ፥ በዓለም ዙሪያ የከፍተኛ የደም ግፊት መጠን እንዲከሰት ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ስርዓት እና ከመጠን ያለፈ የሰውነት ውፍረት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ወስጥ በርካታ ሰዎች በከተሞች አካባቢ መኖር እና በቂ የሆነ የአካል ብቃትን እንቅስቃሴ አለመስራትንም በምክንያትነት ገልጸዋል።

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው ያሉት ሙረይ፥ ቁጥሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም ይጠቅሳሉ።

ይህንን ለማስቆምም የአኗኗር ዘይቤን መቀየር እና አስፈላጊ የሆኑ ህክምናዎችን መውሰድ መልካም መሆኑም መክረዋል።

ምንጭ፦ www.upi.com/Health

 android_ads__.jpg