የተጠበሱ ስጋዎችን መመገብ ከጡት ካንሰር የዳኑ ሴቶችን የመሞት እድል ይጨምራል - ጥናት

አዲስ አበባ ፣ ጥር 1 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የተጠበሱ እና በፋብሪካ የተቀነነባበሩ የስጋ ውጤቶች ለጤና ጠንቅ እንደሆኑ ይነገራል።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ከፍ ባለ የሙቀት መጠን በመጥበሻ የሚጠበስ ስጋ ለጡት ካንሰር እንደሚያጋልጥ ያሳያሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በአሜሪካ የሰሜን ካሮላይና ዩኒቨርሲቲ ጥናት ተደርጓል።

የአሁኑ ጥናት ደግሞ የተጠበሰ ስጋ መመገብ፥ ከጡት ካንሰር ህመም የተፈወሱ ሴቶችን እንደሚጎዳ ይገልጻል።

ምክንያቱ ደግሞ ይህ አይነት አመጋገብ ከበሽታው የዳኑ ሴቶችን ዳግም ለችግሩ ያጋልጣቸዋል የሚል ነው።

ከጡት ካንሰር ከዳኑ በኋላ ረጀም እድሜ ለመቆየት ታዲያ ይህን አይነቱን አመጋገብም ማስወገድ ይገባል ብለዋል የጥናት ቡድኑ አባላት።

ምክንያቱም ከበሽታው ተፈውሰው ይህን አመጋገብ የተከተሉ ሴቶች በዚህ ችግር በድጋሚ የመያዝ እና የመሞት እድላቸው ከፍተኛ ስለሚሆን ነው ብለዋል።

የተጠበሰውን ስጋ በሚመገቡ ጊዜ የሰውነትን ዲ ኤን ኤን የሚቀይሩ ኬሚካሎች በሰውነት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ስለሚመረቱ መሆኑንም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

እነዚህ የሚመረቱ ኬሚካሎች ደግሞ ካንሰርን የሚያስፋፉና የሚከሰተውን ችግር የሚያሳድጉም ናቸው።

የጥናት ቡድኑ አባላት ለዚህ እንዲረዳቸው 1 ሺህ 508 ሴቶችን በጥናታቸው አካተዋል።

ለዚህም የእነዚህን ሴቶች የአምስት አመት አመጋገብ ለማየት ሞክረዋል።

በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ታዲያ 597ቱ ለህልፈት መዳረጋቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ውስጥ ደግሞ 237ቱ ከጡት ካንሰር ጋር በተያያዘ መሞታቸውንም ነው የገለጹት።

ይህም በከፍተኛ ሙቀት በመጥበሻ የተጠበሱ ስጋዎችን ከመመገብ ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

በመጥበሻ ተጠብሰው የሚዘጋጁት የጥጃም ሆነ የበሬ ስጋዎችን አብዝቶ መጠቀሙም፥ ሴቶችን ከጡት ካንሰር ከተላቀቁ በኋላ ዳግም ለዚህ ችግር ያጋልጣቸዋል።

ይህን አብዝተው የሚመገቡት ከማይመገቡት ይልቅ፥ በ23 በመቶ ደግሞ በድጋሚ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ናቸው፤ ይህ ደግሞ በጊዜ ሂደት ህይዎትን እንደሚነጥቅም ያስረዳሉ።

ከዚህ ባለፈ ግን ከጡት ካንሰር መዳን በኋላ ይህን አመጋገብ የሚከተሉት በ31 በመቶ ጊዜያቸውን እያሳጠሩም ነው ይላሉ።

 

 

ምንጭ፦ medicalnewstoday.com/

 

android_ads__.jpg