በደም ምርመራ ብቻ አንድ ሰው ምን ያክል እድሜ እንደሚኖር መተንበይ ችለናል- ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ፣ ጥር 1፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደም ምርመራ ብቻ አንድ ሰው በምድር ላይ ምን ያክል እድሜን እንደሚኖር ቀድመን መተንበይ ችለናል ሲሉ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

እንዲህ አይነት ነገሮች በሳይንስ ነክ ልበወለዶች ላይ እንጂ በእውን ተሰምቶ አይታወቅም ነበር፤ አሁን ግን የቦስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ይህን እውን አድርገናል እያሉ ነው።

ተመራማሪዎቹ ይፋ ባደረጉት አዲስ የጥናት ውጤትም በደም ምርመራ ብቻ የአንድን ሰው አጠቃላይ የምድር ላይ ቆይታ የእድሜ መጠንን ለመተንበይ እንደቻሉ ነው የሚናገሩት።

ጥናቱን ከ5 ሺህ ሰዎች በተሰበሰበ የደም ናሙና ላይ የተካሄደ ሲሆን፥ በአጠቃላይ ስምንት ዓመታተን እንደፈጀም ነው የሚናገሩት።

ተመራማሪዎቹ በጥናታቸው የተሳታፊዎቹን መልካም እና መጥፎ አጋጣሚዎች ላይ ክትትል ያደረጉ ሲሆን፥ በተለይም ከእድሜ ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ እንደ ለልብ ህመም፣ ለካንሰር እና ለስኳር በሽታ ተጋላጭነታቸውን ተመልክተዋል።

በዚህ ጥናትም የሰዎችን እድሜ ቆይታ ለመለየት የሚረዱ 26 ዓይነት ምልክቶችን ማግኘታቸውንም አስታውቀዋል።

የጥናቱ ውጤትም ሰዎች ለእነዚህ የህመም አይነቶች ተጋላጭ መሆናቸውን ቀድመው እንዲያውቁ የሚረዳ ሲሆን፥ ከበሽታዎቹ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮችን ለመከላከልም ይረዳል ተብሏል።

የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶክተር ፓዎላ ሴባስቲያኒ እና ዶክተር ቶማስ ፔርልስ፥ የጥናቱ ውጤት የሰዎች እድሜ መካከል ልዩነት ለምን ተፈጠረ የሚለውን ለማወቅ ያስችላል ብለዋል።

እንዲሁም የሰዎችን እድሜ ቀድመን መተንበይ መቻላችን፤ ሰዎች ያሉባቸውን ችግሮች ቀድመው እንዲያውቁ በማድረግ ረጅም እና ጤናማ እድሜን እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚረዳም ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል።

ጥናቱ በተለይም የሰዎች የሞት መጠን ለምን ይጨምራል የሚለውን ለመለየት አስችሏል ያሉት ተመራማሪዎቹ፥ ለሰዎች ሞት ምክንያት ከሆኑት እና ቀድሞ ለመተንበይ ከሚያስችሉት ወስጥ ደግሞ አንዱ የልብ ህመም ነው ሲሉም ያብራራሉ።

አሁን በተሰራው ጥናት ላይ በመመርኮዝም አንድ ሰው እድሜው በምን ሁኔታ እየሄደ ነው የሚለውን እና ከአድሜ ጋር ተያይዘው ሊያጋጥሙት የሚችሉ የጤና እክሎችን ቀድሞ መተንበት መቻሉንም አብራርተዋል።

በብዙ ሰዎች ላይ በመሰራት የተገኘውን የጥናት ውጤት ለማረጋገጥ አሁንም ብዙ ጥናቶች ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/health

android_ads__.jpg