ቻይናውያን ተመራማሪዎች የጨረር መሳሪያ መስራታቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 3 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይናውያን ተመራማሪዎች የጨረር መሳሪያ መስራታቸውን እየገለጹ ነው።

ማንነታቸው ያልተገለጸው ተመራማሪዎች ኢላማውን ከረጅም ርቀት የሚመታ የጨረር መሳሪያ መስራታቸውን ገልጸዋል።

ዜድ ኬ ዜድ ኤም 500 የተሰኘው የጨረር መሳሪያ ከ804 ሜትር ኢላማውን መምታት እንደሚችልም ነው ተመራማሪዎቹ የገለጹት።

መሳሪያው ኢላማውን ከተጠቀሰው ርቀት ላይ የሚመታ ሲሆን፥ ኢላማው ላይ ካረፈ በኋላም ኢላማውን በማቀጣጠል ያወድማል።

ይህ የጨረር መሳሪያ የመታውን ኢላማ በአጭር ጊዜ በማቀጣጠል ከጥቅም ውጭ ያደርጋልም ነው የተባለው።

ተመራማሪዎቹ እንዳሉት መሳሪያው ሰው ላይ ቢተኮስና ኢላማውን ቢመታ የተመታው ሰው በመሳሪያው ህይዎቱ አያልፍም።

ከዚያ ይልቅ መሳሪያው የመቀጣጠል ባህሪ ስላለው ያረፈበት ቦታ ላይ በመቀጣጠል በደቂቃ ውስጥ ኢላማውን የማንደድ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

ይህ መሳሪያም ዢያን በተባለችው ከተማ የተሞከረ ሲሆን፥ ከተጠቀሰው ርቀት ላይ ኢላማውን በመምታት በእሳት የማያያዝ አቅም እንዳለው ታይቷል።

ይህ የጨረር መሳሪያ በመታበት ፍጥነት የህይዎት መጥፋትና በአቅራቢያው ባሉት ላይ በመዛመት ከፍተኛ የንብረት ውድመት የማያስከትል መሆኑም ይነገርለታል።

ከኤኬ 47 እኩል መጠን ያለው መሳሪያ ባለ 15 ሚሊ ሜትር ሲሆን፥ 3 ኪሎ ግራም ይመዝናል ተብሏል።

አሁን ላይ በምርምር የተሰራውን መሳሪያ በቀጣይ በብዛት የማምረት እቅድ እንዳላቸውም ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

መሳሪያው በሃገሪቱ ለሚካሄዱ ፀረ ሽብር ዘመቻ እንዲሁም እገታ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች ጥቅም ላይ ይውላልም ነው የተባለው።

ይህን መሰሉ የጨረር መሳሪያ ግኝት ግን ለቻይና እና አሜሪካ ሌላ የፍጥጫ መንስኤ እንደሚሆን ተገልጿል።

ይህን መሰሉ መሳሪያ ከሳይንሳዊ ልብ ወለድ ፊልሞች ባለፈ እውን ሆኖ ባያውቅም አንዳንድ ሃገራት ግን እንዳላቸው ይታመናል።

አሜሪካም በፈረንጆቹ 2023 ይህን መሳሪያ ጥቅም ላይ እንደምታውል ከሁለት አመት በፊት መግለጿ ይታወሳል።

የሃገሪቱ ባህር ሃይልም ይህን መሳሪያ ለመታጠቅ የሚያስችል የምርምር ስራ በ300 ሚሊየን ዶላር ማስጀመሩን ገልጿል።

 

 

 


ምንጭ፦ independent.co.uk/