ማህበራዊ ሚዲያዎች ያለተጠቃሚዎቹ ፍቃድ አድራሻቸውን ይበረብራሉ ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በዓለማችን የሚገኙ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ያለተጠቃሚው ፍቃድ ጂፒኤሱን በመበርበር ብቻ የሚገኙበትን አድራሻ እንደሚመነትፉ ተገለጸ፡፡

ሆኖም ኩባንያዎቹ የመረጃ ደህንነት መተግበሪያ ላይ ያሉበትን ቦታ ያለማሳወቅ መብት ቢሰጣቸውም በጎን በኩል ግን በአፕሊኬሽን በመታገዝ መረጃዎችን ይሰበስባሉ ነው የተባለው፡፡

ይህ ብቻም አይደለም የሰበሰቡትንም መረጃ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው እንደሚሰጡም ተነግሮዋል፡፡

የአይፒ አድራሻ በእንግሊዘኛ አጠራሩ "ኢንተርኔት ፕሮቶኮል" በመባል የሚታወቀው ከኢንተርኔት ጋር ለተገናኘ ማንኛውም ኮምፕዩተር የሚሰጥ በቁጥር የሚገለጽ አድራሻ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ታዲያ እንደ ፌስቡክ ያሉ ማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚው ያለበትን አድራሻ በአይፒ በመታገዝ የተጠቃሚዎችን ጂፒኤስ ይመነትፋሉ ተብሏል፡፡

በተጨማሪም ፌስቡክ የፍለጋ ታሪኮዎን እንዲሰርዙ ይጠይቆታል እርሶም ፍላጎቶት ከሆነ ያጠፉታል ሆኖም እርሶ ካሉበት ገጽ ላይ የጠፋ ቢመስልም ኩባንያው ግን ባዘዙበት ቅጽበት ሳይሆን የግሎን መረጃ ከስድስት ወራት በኃላ አዘግይቶ ነው የሚሰርዘው ተብሏል፡፡

እነዚህ ኩባንያዎች መረጃዎችን የሚሰበስቡበት ዋነኛው መንገድ በሌሎች አፕሊኬሽኖች በመታገዝ ሲሆን፥ አንዳንዴም የኦንላይን ገበያ አድራሻዎችን በመጠቀም ነው ያሉበትን ትክክለኛ አድራሻ እንደሚያስሱ የተገለፀው፡፡

አማዞን በበኩሉ በትክክል ግልጽ ባያደርገውም መረጃዎችን ከሦስተኛ ወገን ጋር ሊለዋወጥ እንደሚችል ጥቆማ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባለፈው ግንቦት ወር የአውሮፓ ህብረት ጠቅላላ የመረጃ ደህንነት ተቆጣጣሪ ከመረጃ ደህንነትና ከሦስተኛ ወገን ጋር በተያያዘ አንድ ህግ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን፥ ሆኖም መረጃዎችን ለሦስተኛ ወገን የሚስተላልፉ ኩባንያዎች ድርጅቶቹን ተው እንዲያስቀምጡ አያስገድዳቸውም እየተባለ ተተችቷል፡፡

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ
በአብርሃም ፈቀደ